ቀጠናዊ የሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ ልማትና አካባቢያዊ አብሮነት ላይ ያተኮረ  ኮንፈረንስ ተካሄደ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ጥር 25/2016 ዓ.ም ( ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር  በምስራቅ የሀገራችን ክፍል ካሉ ዩኒቨርስቲዎች፣በሱማሌላንድ በሚገኘው የሀርጌሳ እና ጅቡቲ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር  ያዘጋጀው ታላቅ ቀጠናዊ የሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ ልማትና አካባቢያዊ አብሮነት ላይ ያተኮረ  ኮንፈረንስ በድሬዳዋ ከተማ  ተካሂዷል።

ኮንፈረንሱ ''ኢትዮጵያ _ሱማሌላንድና ጂቡቲ  መካከል ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር  ሰላምን ለመገንባትና ሁሉን አቀፍ ልማት ከማረጋገጥ አንፃር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸውን ሚና / "The Role of Higher Education Institutions in Peace-building and Inclusive Development in Ethiopia, Djibouti and Somaliland." /በሚል  መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱአለም በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ህዝቦች  የጋራ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስራቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው  ይህ ቀጠና  ለእኛ ሀገር ትልቅ የኢኮኖሚ  ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ትስስራችንን አጠናክረን መሄድ ይኖርብናል ብለዋል።

የዚህ ኮንፈረንስ ዓላማ በቀጠናው የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ላይ ያላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል ነው ያሉት ክቡር አቶ ብናልፍ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን  የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሃይል  ወደ ጥቅም በመለወጥ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን  የአካባቢው ዩኒቨርሲቲዎች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

 

ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም የሰላም ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲ የጋራ ፎረም በመመስረት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትስስር በመፍጠርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር  ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ  ገልፀው ከምስራቁ ቀጠና በተጨማሪ በምዕራቡ በኩል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው እኛ የምንገኘው ብዙ ጊዜ ቀውስ በማይጠፋበት እና አሸባሪዎች በሚበዙበት የአፍረካ ቀጠና እንደመሆኑ መጠን ዘላቂ ሰላማችንን ለማስፈንና  እና የጋራ ልማታችንን ለማረጋገጥ ከጉረቤት ሀገሮች ጋር  በቅርበት እና በትስስር  ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ይህ ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትን የበለጠ የሚያጠናክርና የጋራ የሰላምና የኢኮኖሚ ስራዎችን ለማከናወን እና  ተቀራርበን ለመስራት ሚናው ከፍተኛ ነው  ያሉ ሲሆን በቀጠናው  የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምር እና በፅሁፍ ስራቸው ለቀጠናዊ ሰላምና የጋራ ልማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የሚኖሩ ህዝቦች የጋራ ታሪክ፣ባህል፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት ፣ ተመሳሳይ መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው መጠን  በቀጣይ ከምሁራን ግንኙነት ባሻገር  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዶ/ር ከይረዲን  ገልፀዋል። 

በኮንፈረንሱ ላይ በምስራቅ አፍሪካ ስላለው የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ፣የጋራ ዕድሎችና ስጋቶችና መፍትሄዎች በሚል ርዕስ ፅሁፍ  ከሱማሌላንድ ሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ በመጡት ዶ/ር ናስር ሞሃመድ፣ በአምባሳደር አብዱላዚ አህመድ፣ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በመጡት በፕ/ር ጀይላን ዋልይ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡት  ፕ/ር ገብሬ ያንቲሶ በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።