የሰላም ሚኒስቴር ታሪክ

      

            የሰላም ሚኒስቴር ታሪክ

የሰላም ሚኒስቴር ታሪክ የሰላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራስያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀፅ 13 ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋቋመ፡፡ በመቀጠልም በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እንደገና ተቋቁሟል፡፡ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል የሠላም የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና የንቅናቄ ስልቶችን በመንደፍ ስራ የመስራትና በፌዴራልና በክልሎች መካካል በመገግባባትና በአጋርነት ላይ የተመሰረተ የመልካም ግንኙነት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ተቀምጧል። የሰላም ሚኒስቴር የህዝብ ሰላም መጠበቁን ለማረጋገጥ አግባብነት ካላቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል። በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል ሠላም እንዲሁም የመተባበር ባህል እንዲዳብር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልቶችን ቀይሶ ይተገብራል፤ ከባህልና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራት ሠላምን የማስፈን ስራ ይሰራል። ለሰላም መከበር ከተለያዩ ሀይማኖቶችና ዕምነቶች ተከታዮች እንዲሁም አግባብነት ካላቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል።

፩ የሰላም ሚኒስቴር የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፦

ሀ/ ከሰላም ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ህጎችን ለማውጣት የሚያስችሉ ሀሳቦችን ያመነጫል፣ ሲፀድቁም በስራ ላይ ያውላል፤

ለ/ የሀገር ውስጥ ሰላምን ለማስጠበቅ አግባብ ካላቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል፤ የሀገርና ሕዝብ ሰላም እንዲከበር የሚያስችል ስልት ይነድፋል፤ የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራዎችን ያከናውናል፤

ሐ/ በተለያዩ ኃይማኖቶችና እምነቶች ተከታዮች፣ እንዲሁም በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ሰላምና መከባበር እንዲሰፍን ለማድረግ አግባብ ካላቸው የመንግሥት አካላት፣ የባህልና የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከሌሎች አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፤

መ/ በኃይማኖት፣ በብሔርና ሌሎች ምክንያቶች ሽፋን የሚደረግ የአክራሪነትና የጽንፈኛነትን አስተሳሰብ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን ይቀይሳል፣ ያስፈጽማል፤

ሠ/ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አግባብነት ያላቸውን አካላት ያስተባብራል፤ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመንግሥት ያቀርባል፤ ሲወሰንም አፈጻጸሙን ይከታተላል፤

ረ/ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን የሚያጎለብት የባህል ልውውጥ፣ የስነ-ዜጋ ትምህርት የሚስፋፋበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤

ሰ/ በህብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና ንቅናቄ ስልቶችን ይቀይሳል፣ አተገባበሩን ይከታተላል፤

ሸ/ ለአካባቢያዊ ግጭቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ይለያል፤ ኅብረተሰቡ ወደ ግጭትና አለመረጋጋት እንዳያመራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያመለክት ጥናት ያቀርባል፣ ሲወሰንም ተግባራዊ ያደርጋል፤

ቀ/ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል በመግባባትና በአጋርነት ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር በማድረግ የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የግንኙነቱ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፤

በ/ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 48 እና 62 (6) እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች ያመቻቻል፤

ተ/ አግባብነት ያላቸው ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከክልሎች ጥያቄ ሲቀርብ በክልሎች ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በዘላቂነት የሚፈቱበትን መፍትሔ ይቀይሳል፣ ተግባራዊ ያደርጋል፤

ቸ/ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ሲወሰን አፈጻጸሙን ያስተባብራል፤

ኀ/ የሃይማኖት ድርጅቶችን ይመዘግባል፤