የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር ከሰላም ሚኒስቴር ጋር አብረው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር ከሰላም ሚኒስቴር ጋር አብረው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር አመራርና አባላት ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ክቡር አቶ መሀመድ ማህበሩ እያበረከተ ላለው አስተዋፅኦ ዕውቅና ሰጥተው ማህበሩ እየሰራቸው ካሉ ስራዎች በተጨማሪ ሀገርን በመገንባት ሂደት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለመወጣት ከማህበሩ ብዙ እንደሚጠበቅ አንስተዋል። ማህበሩ በተለይ በኩሪፍቱ ዲክላሬሽን መሠረት ለወል ትርክት ግንባታ ስኬት የበኩሉን ለመወጣት የገባውን ቃል ኪዳን ለማክበር እንዲሰራም ሚኒስትሩጠይቀዋል።
የሰላምግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማሳካት መንግስት በህብረተሰቡ ዘንድ የወል ትርክትን ማስረፅ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ሂደቱን በባለቤትነት ከማከናወንአንፃር የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት በጥናት ላይ ተመስርቶ ከማህበሩ ጋር ለመስራት ማሰቡን ተናግረዋል። የታሪክ ምሁራን ለጠንካራ ሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚናንም ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደሚገነዘብም በመጠቆም።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሳካቸውን ዋና ዋና ውጤቶች ያስተዋወቁ ሲሆን በዋናነትማህበሩ መቋቋሙ፣ ታግዶ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታሪክ ትምህርት እንዲጀመር በመደረጉ፣ ትክክለኛ እና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ታሪክን ማስረጽ ላይ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል ።
ቀጣይ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል በጥናት መመለስ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ሁለቱም ተቋማት በጋራ በሚሰሯቸው ስራዎች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረምም ተስማምተዋል ።
በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት የወል ትርክት ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና መሠረት በማድረግ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀትም መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሰላም ለኢትዮጵያ!