የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ወይይት ተካሄደ
የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ወይይት ተካሄደ
ሚያዝያ 08 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የዴሞክራሲ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ክቡር አቶ ፍቃዱ ተሰማ በተገኙበት የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ወይይት ተካሂዷል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡ ሲሆን መንግስት ቅርብና የግልፀኝነት ስርዓትን ስለሚከተል ይህ የመንግስት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለሰራተኛው እንዲቀርብ ሆኗል ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያና ለኢትዮጵያ ያለው አንድምታ፣የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሪፎርም አፈፃፀም ውጤቶችና አዝማሚያዎች፣ የዋና ዋና የመሠረተ ልማት እና ፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ዘላቂ ማህበራዊ አካታችነትና ሰብዓዊ ልማት፣የመንግስት አገልግሎት ሪፎርም እና የማስፈፀም አቅም ግንባታ እና መሰል ጉዳዮች ላይ እንደ ሀገር የተገኙ ውጤቶች ላይ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል።
በተጨማሪም የሰላም ሚኒስቴር ተቋማዊ የሪፎርምና የማስፈፀም አቅምን ከማሳደግ፣ ዘላቂ ሰላም ከመገንባት ፣ ገዥ ትርክትን ከማስረፅ ፣ግጭትን አስቀድሞ ከመከላከልና ከመፍታት፣ የፌዴራል ስርዓቱን እና የመንግስታት ግንኙነትን ከማጠናከር አንፃር ባለፋት ዘጠኝ ወራት የተሰሩ ሥራዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን አቅርበዋል።
ከሰራተኞች ለተነሱ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ ማብራሪያ የሰጡት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ክቡር አቶ ፍቃዱ ተሰማ በማክሮ ኢኮኖሚ ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን መጠናከር ለብዙ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል ብለዋል፡፡
አክለውም የብሔረ መንግስት ግንባታ አለመጠናቀቅ የሀገራችን ትልቁ ችግር ነው ያሉ ሲሆን የሰላም ሚኒስቴር ገዥ ትርክት ላይ ትኩረት አድርጎ የሰዎችን አስተሳሰብ በበጎ መልኩ ለመገንበት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
ሁሉም ማህበረሰብ ብሔረ መንግስት ግንባታ ላይ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።