የሰላምና የልማት ፎረሙ አንድነትን የሚያጠናክር የጋራ ልማትና ብልጽግናን የሚያሳካ ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17 ቀን 2017(ኢዜአ)፡- የአፋርና ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች የሰላምና የልማት ፎረም አንድነትን የሚያጠናክር እንዲሁም የጋራ ልማትና ብልጽግናን የሚያሳካ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲካሄድ የቆየው የሱማሌና አፋር ክልሎች ሕዝቦች የወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክ 12 አባላት ያሉት "የአፋርና ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች የሰላምና የልማት ፎረም" በማቋቋም ተጠናቋል።

የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሰው ልጅ ምንም አይነት ልዩነት ቢኖረው ከተቀራረበ ችግሮቹን መፍታት እንደሚችል ያሳየ ውይይት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ውይይት መሆኑን ያምናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በራሳቸው ፍላጎት የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የአፋርና ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች አንድ የሚያደርጋቸውና የሚያጋምዳቸው ብዙ መሆኑን ገልጸው፤ የህዝቡ ፍላጎት በጋራ መልማት መሆኑን ተናግረዋል።

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የትናንት ጥያቄ ሰላም እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በመድረኩ የታየው የሰላም ቁርጠኝነት የነገ ፍላጎታቸው በጋራ መልማትና መበልጸግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሰላምና የልማት ፎረሙ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት መወያየታቸውንም ተናግረዋል።

መንግስት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፋርና ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች የሰላምና ልማት ፎረም ሰብሳቢ ሙሳ አደም በበኩላቸው፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተከስቶ የነበረውን ችግር መፍታት የሚያስችል መፍትሄ ከህብረተሰቡ መምጣት እንዳለበት ታምኖ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

መድረኩ ምሁራን ሴቶች ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ተስፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

በውይይቱ ያለፈውን ጥፋት በቁጭት የነገውን የጋራ ሰላምና ልማት በተስፋ ማየት የሚያስችል ትብብር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፣ የሶማሌና አፋር ክልሎች አመራር አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የኢፍጣር መርሃ ግብር ተካሂዷል።

#ኢዜአ