ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ ታላቁ ሩጫ ሊካሄድ ነው
ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ ታላቁ ሩጫ ሊካሄድ ነው
የሰላም ሚኒስቴር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ቃል ሰፊ ሀገራዊ የሩጫ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
ከቀበሌ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ 15 እንደሚጠናቀቅ በሚጠበቀው ታላቅ ሀገራዊ የሰላም የሩጫ መርሀ ግብር እቅድና አተገባበር አስመልክቶ የሰላም ሚኒስቴር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች የሰላምናፀጥታ እና የስፖርት ዘርፍ አመራሮች ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ መድረክ የሰላም ሚኒስቴር ዴዔታ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ እንዳሉት ዜጎች የሰላም ባለቤት መሆናቸውን ግንዛቤ ለመፍጠርና በዜጎች መካከል የበለጠ መቀራረብ ለመፍጠር በማሰብ ታላቁ የሰላም የንቅናቄ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። ዝግጅቱ በሰላምና ፀጥታ መዋቅሮች አስተባባሪነትና ከስፖርት ዘርፎች በቅንጅት በመከናወን ሰኔ 15 በመላው ሀገሪቱ በተመሳሳይ ቀን ሚሊዮኖች በሚሳተፉበት የ5000 ሜትር ታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ስፖርትን ለሰላም በመጠቀም ዜጎች ለሰላም ዘብ እንዲሆኑ ለማስቻል የሰላም ሚኒስቴር የወሰደው ተነሳሽነት እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው የተቋማት ቅንጅት ለዚህ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ የሁለቱ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙ የሰላምናፀጥታ እና የስፖርት ዘርፍ አመራሮች በበኩላቸው ንቅናቄው ሀገራዊ ሰላሙን የበለጠ ለማፅናት እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ስለሚረዳ ለስኬቱ በሙሉ ተነሳሽነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።በንቅናቄ የሩጫ መርሀ ግብሩ 20 ሚሊየን ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።