አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ንቅናቄ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ።

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ንቅናቄ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ።

የካቲት 22/2016 ዓ.ም 

“አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ”  ሀገር አቀፍ  ንቅናቄ  ማጠቃለያ መርሐ-ግብር ተከናወነ።

የሰላም ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በትብብር  “አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ  በመጠናቀቁ  በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም  የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ተፈጽሟል።

በሀገር አቀፍ ንቅናቄው ላለፉት ሁለት ወራት 128ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በማድረግ ኢትዮጵያዊያን ለጋራ ታሪካቸውና ማንነታቸው፣ ለአንድነታቸው እና ሀገራዊ ጥቅም ፣  ሁሉንም በሚያጋሯቸውና በሚያስተሳስሩ  እሴቶች ላይ በስፋት ውይይት ሲያደርጉ እንደቆዩ ተገልጿል።  

የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ  በመድረኩ ተገኝተው  ንግግር ያደረጉ ሲሆን "የአድዋ ጀግኖቻችንን ከየቦታው ነቅሎ አውጥቶ እንዲዘምቱ ያደረገው የእናት ሀገር ፣ የዜጎች ፣ የሃይማኖትና የነጻነት ፍቅር ነበር። ይህም ፍቅር  ራስን ለሀገር ለወገን የመሰዋት እንጂ ለራስ ጥቅም ሀገርን እና ወገንን የመሰዋት አይደለም" በማለት   ድሉ በኢትዮጵያዊያን የተፈጸመ የአፍሪካዊያንና የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

"እኛ በዚህ ዘመን የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በአድዋና በሌሎች የትግልና የመስዋእትነት ስፍራዎች ተዋድቀው ነጻነቷን ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር የገጠሟትን እና ወደፊትም የሚገጥሟትን ችግሮች ተጋፍጠን እያሸነፍን ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላሟ የበዛ እና ብልፅግናዋ የተረጋገጠ ሀገር እንድትኖረን የሚያስችል የራሳችንን አሻራ ማስቀመጥ አለብን" ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

 

"ወጣቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሀገር ግንባታ ካላቸው ወሳኝና የማይተካ ሚና አንጻር ከመጪው ጊዜ ጋር ከወዲሁ እንዲተዋወቁ ፣ በሁሉም መስክ ብቁና ዝግጁ እንዲሆኑ፣ አድዋንና ሌሎች የሀገራቸውን ታሪክ እና ማንነታቸውን  በትክክል እንዲያውቁ በማድረግ  ምሁራን በተገቢው ሁኔታ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትር ክቡር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)  አስገንዝበዋል።

 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)  "ሁላችንም ከአያቶቻችን በወረስናቸው እንደ አድዋ በመሳሰሉ ተላላቅ ድሎችና ማህበራዊ እሴቶች የልጆቻችንን ስብእና በማጎልበት የዛሬው ትውልድ በጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ በተራው የሚዘከርበት የራሱ ወርቃማ የድል ታሪክ ገድል እንዲሠሩ ልናደርግ ይገባል" ብለዋል።

 

ዛሬ ማጠቃለያ በተደረገው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፣ ማኅበረሰቦች፣ የፖሊስ አካላት፣ የሰላም መዋቅሮች፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት እና ተቋማት ተሳትፈው በሰላም፣ በሀገር ግንባታና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

 

ንቅናቄው በስኬት እንዲጠናቀቅ ለተባበሩት እና አስተዋጽዖ ላደረጉት ሁሉ ተቋማቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡