ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የሀገርና የሕዝብ ፍቅር በማሳደግ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው ተባለ
ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የሀገርና የሕዝብ ፍቅር በማሳደግ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው ተባለ
መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለ12ኛ ዙር በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስልጠና የወሰዱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመረቁ፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ እስማኤል አሊሴሮ “ፕሮግራሙ ወጣቱን በአመለካከትና በሥነ-ምግባር እንዲታነጽ ከማድረግ ባሻገር ብቁ ዜጋን ማፍራት የሚያስችል፤ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ወጣቶች ሀገራቸውን እና ማኅበረሰባቸውን እንዲያውቁ የሚያደርግ እና የሀገር ፍቅር ስሜት በውስጣቸው እንዲሰርጽ የሚያደርግ ስለሆነ በተሰማሩበት ሁሉ ማኅበረሰብን በማገልገል ለታዳጊዎችና ለሌሎች ወጣቶች መልካም አርአያ የሚሆኑበት ነው” ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ እስማኤል የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሀገር ግንባታ ሥራው ወጣቱን በስፋት የማያሳትፍ ከሆነ ዘላቂነት እንደማይኖረው በማስገንዘብ ወጣቱ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆችን በውል ተገንዝቦ ለትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት እና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ የሚያስወግድ ብሎም የወጣቶችን የሀገር እና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንት ተወካይ ገ/ኪዳን ተስፋይ (ዶ/ር) “ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ኢትዮጵያዊያን ርስ በራሳችን የምንተዋወቅበት፣ የመተጋገዝ፣ የመደጋገፍና የመተባበር ባህላችንን እና እሴቶቻችንን የምናዳብርበት ነው፤” ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ፕሮግራሙ ወጣቱን ከሕዝብ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ከሕዝቡ ዘንድ ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንዲያውቁት በማድረግ ለሰላም፣ ለሀገር ግንባታ እና ለልማት ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት የትግራይ ክልል ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሽ ሱባጋዲስ ናቸው፡፡ አቶ ሀይሽ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ለተሳታፊ ወጣቶች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት በጎ ፈቃደኞችን በሥነ ምግባር፣ በክሕሎት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በሥራ ፈጠራ ግንዛቤ የሚያዳብር ስልጠና በመስጠት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ወጣቱን በሀገር ግንባታ የማሳተፍ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ መሆኑን የስልጠና ማዕከሉ አስተባባሪ አቶ አብርሃ ደስታ የስልጠና ሂደቱን አስመልክተው ባቀረቡት ማብራሪያ አስገንዝበዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞችም በሚሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት በሰላም ግንባታ የሰላም አምባሳደርነት ሚና በመወጣት በሀገር ግንባታው የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተገልጿል፡፡