ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርአቶች ለሰላም ያላቸው ፋይዳ
ባህላዊ ግጭት አፈታት ስርአቶች ለሰላም ያላቸው ፋይዳ
በሀገራችን በሁሉም አከባቢዎች ሰዎች በሚያደርጎቸዉ ማህበራዊ መስተጋብር ዉስጥ ግጭት የማይቀር አንድ ክስተት ሲሆን በሀገራችን ይህንን የሚፈታ በርካታ የግጭት አፈታት ስርአቶች ያሏት፡፡
በሀገራችን የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏቸውን የግጭት አፈታት ስርአቶች ብንመለከት ግጭት ውስጥ በገቡ ወገኖች መካከል እርቅ እንዲወርድ በማድረግ የተወሰነ ሳይሆን፤ ለግጭት ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ በማህበረሰቡ ዘንድ በግጭቶች ምክንያት ደፍርሶ የነበረውን ሰላም መልስ እስኪያገኝ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን በዚህም በግጭት ምክንያት የተቋረጡ ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸውን በመጠገን በማህበረሰቡ ዘንድ ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ስለሆነም በአገራችን የተለያዩ ማህበረሰቦች የሚገለገሉባቸው የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን በሀገራችን ከሚገኙ የእርቅ አፈታት ስርዓቶች መካከል በአማራ ክልል በወሎ አካባቢ የሚገኘውን የ"አባጋር" ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ለሰላም ያለውን ፋይዳ ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡
የአባጋር ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት
******************
አባጋር በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ረጅም ታሪክ፣ ገናና ስምና ሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው የግጭት ማስወገጃ ተቋም ነው፡፡ አባጋር የሚለው ቃል ‹‹አብ›› እና ‹‹አገር›› የሚሉትን ቃላት በማጣመር የተገኘ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹የአገር አባት›› ማለት ነው፡፡ አባጋር የሚለው ስያሜ፣ የአገር ሽማግሌ ወይም የመሪ የማዕረግ ስም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕግ፣ ደንብ፣ ልማድና ባህል ማለት ነው፡፡አባጋርነት ከአባት ወደ ልጅ በሚተላለፍ መንፈሳዊ ብቃትና ወግ የሚገኝ ሥልጣን ሲሆን በደቡብና ሰሜን ወሎ በሚገኙት አብዛኞቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የየራሳቸው አባጋር አላቸው፡፡
ይህ አባጋርም የተጣላን ያስታርቃል፣ የተበደለን ያስክሳል፣ በድብቅ የተሠራ ወንጀልን ያወጣል፤ ደም ያደርቃል፡፡ አባጋር በአጭሩ እንደዛሬው ወንጀልን የሚከላከልና የሚመረምር ፖሊስ በሌለበት ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ ወንጀለኛ ስለወንጀሉ በአገር ልማድና ሕግ እንዲጠየቅ፣ ቂም በቀል ያለባቸው እርስ በእርስ እንዳይጠቃቁ ዋስትና ይሆን ዘንድ የአገሬው ሰዎች የፈጠሩት ነባር አገር በቀል ተቋም ነው፡፡
አባጋር በማህበረሰቡ ውስጥ ባለው ተቀባይነት፣ ታማኝነትና ክብር ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታትም ሆነ አሁን አገሪቷን በሚያስተዳድረው ሥርዓት ዕውቅና የተሰጠው አገር በቀል የግጭት መከላከያና መፍቻ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህም አባጋሮች ወንጀልን በመከላከልና ወንጀለኛን በማውጣት፣ እንዲሁም ሰላምን በማስፈን ረገድ ከቀበሌ መስተዳድር አካላትና ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ይሠራሉ፡፡
አባጋሮች ሕግን የሚያስከብሩበት እርቅ የሚያወርዱበት ወይም ወንጀለኛን የሚያወጡበት መንፈሳዊ ሥልጣን ወይም አሠራር ‹‹ቆቲ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹ቆቲ›› ወንጀል በተፈጸመበት አንድ አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ በነቂስ ወጥቶ ወንጀሉን ራሱ/ራሷ ላለመሥራቱ/ቷ ወይም ወንጀሉ በሌላ ሰው ሲፈጸም አለማየቱን/ቷን በመሃላ የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ነው፡፡
የአባጋር ስርአት ሲከናወን ገዳይ ወይም የተገደለበት ቤተሰብ የተለያዩ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ሁሉም በአባጋር ስርአት ይገዛሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የሀገር ወግና ደንብ ባህል ስለሆነ በአባጋር አማካኝነት እርቁ ይካሄዳል፡፡ የክርስቲያን እምነት ተከታይ ቢሆንም መስቀል ይዘዉ አብረውት ካህናት በተገኙበት እርቁ እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡ ይህም በሀገራችን ከሚገኙ አካባቢዎች እስልምናና ክርስትና በመከባበርና በመቻቻል አብሮነትን በማጎልበት አርአያ ከሆኑ አካባቢዎች ወሎ አንዱ መሆኑን ያሳያል፡፡
በሀገራችን በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚገኙ የእርቅ አፈታት ስርአት ካላቸው ባህሪ መካከል እርቅ ከተካሄደ በኋላ መልሰዉ ወደ ነብስ መገዳደልና ጠብ አለመመለሳቸው ነው፡፡ በአባጋር የእርቅ ስርአት የታረቁ ሰዎችም በሸማግሌዎች ፊት ቆመው እርቅ ካወረዱ መልሰው ወደ ፀብ አይገባም፡፡
ምንጭ፡- ከባህልና ስፓርት ሚኒስቴር
ሰላም ለኢትዮጵያ !