ሚዲያዎቻችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ተካሄደ
ሚዲያዎቻችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ተካሄደ
ሰኔ 25/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ''ሚዲያዎቻችን ለዘላቂ ሰላማችን'' በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ አካሂዷል።
በኮንፍረንሱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱአለም የዛሬው መድረክ ዓላማ በሀገራችን የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሚዲያዎቻችን ያላቸውን አወንታዊ እና አሉታዊ ሚና በመፈተሽ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚዲያ የሃሳብ ብዝሃነትን በማስተናገድ ህብረተሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያንሸራሽር ከማድረግ አንፃር ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት ክቡር አቶ ብናልፍ ሚዲያ የሰውን አመለካከት እና ባህሪ በመቅረፅ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ቅን እንዲያስቡ የማድረግ አቅሙም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በአንፃሩ ሚዲያ በአግባቡ ካልተያዘ የጥቅሙን ያህል ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ይህን ደግሞ በአይናችን አይተናል በታሪክም አንብበናል ብለዋል።
ክቡር አቶ ብናልፍ አክለውም የዚህ ዘመን ችግር መረጃ የማግኘት ሳይሆን መረጃን መርጦ የመጠቀም ችግር ነው ያሉ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ደግሞ ተከታታይ ስልጠናዎች እና ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው የሰላምን አስፈላጊነት የሚረዱት በሰላም እጦት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ናቸው ያሉ ሲሆን የሰላም አጀንዳ የሁላችንም አጀንዳ መሆኑን ተረድተን ሁላችንም ኃላፊነት መውሰድ ይኖርብናል ብለዋል።
አቶ መሐመድ እድሪስ አክለውም የሚዲያ ባለሙያዎች የህብረተሰቡን መልካም ግንኙነትና እሴት አጉልቶ በማውጣት ህዝብን የማቀራረብ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ '' ሚዲያና ሰላም በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ'' የሚል ፅሁፍ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በመጡት በአቶ ዴሬሳ ተረፈ በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ውይይቱን የመሩት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃነት ባለበት ሀገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ብዝሃነትን አስጠብቆ ከመሄድ አንፃር ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ለተግባራዊነቱ መትጋት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ክቡር ዶ/ር ከይረዲን አክለውም የሰላም ሚኒስቴር ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተቀራርቦ መስራት የሚያስችለውን የተለያዩ መድረኮችን እያመቻቸም ይገኛል ብለዋል::
በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ፣ማህበራዊ አንቂዎች ፣የማህበራዊ ሚዲያ መሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።