ዘላቂ እና አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የተለያዩ አጋር አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
ዘላቂ እና አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የተለያዩ አጋር አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች በሰሜን አሜሪካ ዩታሀ ግዛት ከሚገኘው የስተርሊንግ ፋውንዴሽን መሪዎች ጋር በሰላም ግንባታ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።በሰሜን አሜሪካ ዩታሀ ግዛት በኢትዮጵያ በተለያዩ የሰላም ግንባታ ተግባራት ድጋፍ እያደረገ ከሚገኘው ስተርሊንግ ፋውንዴሽን አመራሮች ጋር ድጋፉ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት መንገዶች ዙሪያ ለመወያየት በሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም የሚመራው የሚኒስትር መ/ቤቱ አመራሮች ቡድን በግዛቷ መዲና ሳልት ሌክ ከተማ የሚገኙ የሰብዓዊ አግልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች በመከባበርና በሰላም አብረው በአካባቢው ሰላም፣ አብሮነትና መከባበር ለማምጣት የሚያከናውኑት ተግባርና የተገኘውን ውጤት ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም በዚህ ወቅት እንዳሉት በግዛቲቱ በወጣቱና አዛውንቶች እየተሰጠ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአካባቢው ሰላም ለማምጣትና ጠንካራ ግዛት ለመፍጠር ጉልህ አስተዋፅዖ እያደረገ መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ ከዚህ ተግባር እንደሀገር ብዙ እንደምትማርም ተናግረዋል።
የስተርሊንግ ፋውንዴሸን በኢትዮጵያ ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። የፋውንዴሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኒኮል እስተርሊንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ፣ ድንቅ ባህልና የአብሮነት ዕሴት ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀው መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ፋውንዴሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች በዩታሀ ግዛትና በአጎራባች የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ለበርካታ ዓመታት የዕምነት ጉዳያቸውን የሚፈፅሙበት የቤተክርስቲያን ቦታ ችግርን ለመቅረፍ የተዘጋጀውን የቤተክርስቲያን መገንቢያ ቦታ ከከተማው ተቀብለዋል። የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች በግዛቲቱ ከሚገኙ በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከሚሰሩ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በሳልት ሌክ ከተማ የሚገኙ የበጎ አድራጎት መስጫና የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችንም ጎብኝተዋል።