"ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የሕዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሄደ
"ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የሕዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሄደ
ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፦ የሰላም ሚኒስቴር ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የሕዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሂዷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ፓርላሜንታዊ ወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሰቢ የተከበሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት ምንም እንኳን ለቀጣናዊ ትብብር መንግስት ፖሊሲ ቀርፆ በግንባር ቀደምትነት መስራት ቢጠበቅበትም ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የሲቪል ማህበራት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የእምነት ተቋማት እና ሚዲያዎች በመተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል ።
የተከበሩ አምባሳደር ዲና አያይዘውም እንደነዚህ አይነት ተቋማዊ የውይይት መድረኮች በጉዳዩ ላይ ለመስራት፣ ለመመራመር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እንደ ሀገር ጠቀሜታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በዩኒቨርርሲቲዎች እንደዚህ ዓይነት የውይይት መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በአፅንኦት አመላክተዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ አለሙ (ዶ/ር) ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እና ቀጣናዊ ትስስርን ማጎልበት የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ዜጎችና ተቋማት በተለይም ደግሞ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ገልጸው ዩኒቨርሲቲያቸው ይህን ተቋማዊ ግዴታ ለመወጣት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን በዩኒቨርሲቲዎች እንዲህ ያሉ የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸው እንደ ሀገር የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን በማምጣት ሀገራዊ ጥቅሞች ፣ ሀገራዊ ማንነቶች እና ሀገራዊ እሴቶቻችን ላይ የጋራ አረዳድ ኖሮን ተመሳሳይ ግንዛቤ እንድንይዝ በማድረግ በኩል ያላቸው ፋይዳ ትልቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቀረበው መነሻ ፅሑፍ ላይ ሃሳብ አስተያየቶች ቀርበው በእለቱ የክብር እንግዳ የተከበሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳደሪ እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በመድረኩም የሰላም ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የዞን እና የዲላ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
ምንጭ፡-ዲላ ዩኒቨርሲቲ