በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ይረጋገጥ ዘንድ በትኩረት እንደሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
Asset Publisher
ጥር 2 /2016 ዓ.ም በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ያለውን የፀጥታ ችግር በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በሚመለከት በትኩረት የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው::
ክቡር ሚኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ይመጣ ዘንድ እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዲሚገባው አሳስበው፤ ነገር ግን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ሰላምን ማምጣት እንደማይቻል አስረድተዋል።
ጦርነት የትኛውንም ችግር እንደማይፈታና ቀደም ሲል በስሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተውም ሆነ አሁን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ጦር የሚያማዝዙ ሳይሆን በውይይትና በድርድር ሊፈቱ እንደሚችሉም አብራርተዋል።
ኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር ለመደራደር መንግስት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርጎ ያልተሰካ ቢሆንም፤ የተፈለገው ሰላም እስኪሰፍን መንግስት ለውይይት ዝግጁ እንደሆነ ነው አቶ ብናልፍ የተናገሩት።
የጦርነት መቋጫው ድርድር በመሆኑ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂዎች ተጨማሪ ዋጋ ሳይከፈል ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ የሰላም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ክልል በተሰራው ስራ በክልሎቹ የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ በማምጣት ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ብናልፍ ጠቁመው፤ ዘላቂ ሰላም እስኪመጣ ቀጣይነት ያለው ስራ ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ተላቃ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ይረጋገጥ ዘንድ የሰላም ሚንስቴር የ 10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ለመተግበር ዝግጅት ላይ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል::
ከዚህ በፊት የሰላም አምባሳደር የሆኑ ወጣቶችን አሰልጥኖ በየክልሉ የማሰማራቱ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ምንጭ፡- የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፌስቡክ ገፅ