የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ
የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ታህሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ አካሄዷል፡፡
በመድረኩ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ሀገር ሰላም የምትሆነው እያንዳንዱ ማህበረሰብ ሰላም ሲሆን እንደሆነ ገልፀው የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ ያላቸው ተደራሽነት ሰፊ በመሆኑ ሰላምን ለመገንባት ትልቅ አስተዋፆ አላቸው ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ሰላምን መገንባት የምንችለው ሊፈጠር የነበረን ግጭት ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ ወደ ሰላም መመለስ ስንችል ነው ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንም ያላችሁን ተቀባይነት በመጠቀም ባላችሁ የቋንቋ ተደራሽነት ሰላም ቋንቋ እስኪሆን ድረስ ልትሰሩ ይገባል በማለት ገልፀዋል በቀጣይ ሦስቱም ተቋማት የጋራና የተናበበ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚዲያ ክትትልና አቅም ግንባታ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው ተቋማችን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በሰላም ግንባታ ዙሪያ መስራታችን በሀገራችን ሰላም ግንባታ ሂደት የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን እምቅ ማህበረ-ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም ሰላምን መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ሀገራዊ ሰላምን ሊያረጋግጡ ይገባል በማለት ገልፀዋል ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ስልጣን እና ተግባር ፤ እስካሁን ተቋሙ ያከናወናቸው ተግባራት በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ በሆኑት በአቶ አዱኛ በቀለ ለውይይት ቀርቧል፡፡
የሃይማኖት አባቶችን ፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ፣ ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎችን በመጠቀም እንዲሁም ሰላምን የሚሰብኩ አጫጭር መልዕክቶችን በማዘጋጀት ሰላምን መገንባት እንደሚቻል የውይይቱት ተሳታፊዎች ገልጸው የሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስን ጨምሮ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ኃላፊዎች ፣ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ሥራ አስፈጻሚዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡