እሴቶቻችንን ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ ሀገራዊ አንድነትና ማኅበራዊ ትስስርን ለማስፈን የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡
እሴቶቻችንን ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ ሀገራዊ አንድነትና ማኅበራዊ ትስስርን ለማስፈን የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡
ግንቦት 11/2016 ዓ.ም የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት 10ኛ ዙር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና መርሐ-ግብር መክፈቻ ሥነ-ስርዓት በሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ ተከናውኗል፡፡
የመክፈቻ መርሐ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገመቺሳ ኢትቻ የሰላም በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖትና በሌሎች ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር የሚያሳድግ መሆኑን እና ርስ በርስ የተጋመዱ ማኅበረሰቦች እንዲፈጠሩ በማድረግ አዎንታዊ ሰላምን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ገመቺሳ "የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲገነዘብ በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ብሎም ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት መጠናከር እና ብሔራዊ መግባባት የጎላ ሚና ያለው ስለሆነ በዚህ ሀገራዊ ፕሮግራም የራሳችሁን አዎንታዊ አሻራ በማሳረፍ የዜግነት ኃላፊነታችሁን ለመወጣት መዘጋጀታችሁ ዕድለኝነት እና የህሊናና የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ተግባር ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
ሳሙኤል ጅሎ (ዶ/ር) የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ባሰሙት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር “እኛ ኢትዮጵያዊያን የባህል፣ የቋንቋ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የመልክዓ-ምድር እና የመሳሰሉትን ብዝኃነት የታደለን መሆናችን ለሰላም ግንባታ ምቹ ዕድል እንዳለን ሁሉ ፈተናዎችም ሊኖርብን ስለሚችል ብዝኃነታችንን በጥንቃቄ ይዘን አንዱ የሌላውን ልዩነት አክብረን፣ ልዩነት ጸጋ እንጂ ስጋት እንዳልሆነ ተገንዝበን፣ የኔ አስተሳሰብ ብቻ ይቅደም ከማለት ተቆጥበን፣ ብዝኃነታችንን አክብረን፣ ልዩነታችን ውበታችን፣ ውበታችንም አንድነታችን ሆነው ለሰላም እና ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተግተን ልንሠራ ይገባል፤” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “የሰላም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተሰማሩበት የሰላም አምባሳደር በመሆን ሌላውን አክብረው መከባበርን እንዲያስተምሩ፤ ሌላውን አድምጠው መደማመጥን እንድያሳዩ እና ችግሮችን በውይይት በመፍታትን የውይይት ባህል እንዲዳብር ለማድረግ የተጣለባቸው አደራ ታላቅ ስለሆነ በታላቅ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ወጣቶች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ስለሚኖራቸው ወሳኝ ሚና ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ በሀገር ግንባታ ውስጥ ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲሳተፉ እና ማኅበራዊ እሴቶችን እንዲያዳብሩ ማስቻል፣ በሀገራችን የዘላቂ ሰላም ግንባታ የወጣቱ ድርሻ የላቀ ስለሆነ በክሕሎት፣ በሥነ ምግባር፣ በሥራ ፈጠራ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ማሳተፍ ትኩረት የሚሰጠውም ጉዳይ በመሆኑ በቆይታቸው ለዚሁ የሚያበቃ ስልጠና የሚሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል።