"ብዝሃነት ለአብሮነት " በሚል መሪ ቃል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊካሄድ ነው
"ብዝሃነት ለአብሮነት " በሚል መሪ ቃል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊካሄድ ነው
ግንቦት 1/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብዝሃነት ለአብሮነት " በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት ስልጠና ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ ተካሄዷል ፡፡
በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት ዘላቂ ሰላምን ከመገንባትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ከመፍጠር አኳያ ጉልህ አስተዋፆ እንዳለው ገልፀው በዚህ የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት በ50 ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የ2ኛ እና የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች የአጭር ጊዜ ስልጠናውን ወስደው ከስልጠና በኋላ ለአንድ ወር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እንደሚሰጡ አስገንዝበዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ስራ አስፈፃሚና የክቡር ሚኒስትሩ ተወካይ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ህብረብሔራዊነትን በተገቢው ከማስተዳደር አንፃር ችግሮች የሚስተዋሉባቸው እንደመሆኑ የክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መስጠት ተማሪዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁና እንዲወዱ ከማድረግ ባለፈ በየአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የሰላም እጦቶችን ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 30ሺህ ተማሪዎችን በመመልመል እና በህብረ ብሔራዊ አንድነት ዙሪያ የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት፤ በክልሎች ዋና ዋና ከተሞች በማሰማራት ተማሪዎች ለሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አስተዋፆ እንዲያበረክቱ ማስቻል የስልጠናው ዋና ዓላማ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣የዩኒቨርሲቲዎች ምክትል ፕሬዘዳንቶች፣ የተማሪዎች አገልግሎት ኃላፊዎችና የተማሪዎች ህብረት አመራሮች በምክክር መድረኩ ተሳታፊ ሆነዋል ።