የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር እየተካሄደ ነው
የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር እየተካሄደ ነው
ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት የሀይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሰላምና የልማት ፎረም አባላትን እና የክልሎቹን የሰላምና ፀጥታ አመራሮች ያሳተፈ የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡
በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ የቆየ ሲሆን ይህ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እየተካሄ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ አሁን ያለው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ሕዝቡን በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስተሳሰር በሚቻልበት አቅጣጫ ላይ የሚመክር መድረክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝም እና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩጌታ ገነነ በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ማኅበረሰቦቹ ግጭት የሚያስከትለውን ጉዳት በውል የሚገነዘቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ችግሮችን በንግግር የሚፈቱበት በዘመናት የተገነባ ማኅበረ-ባህላዊ ሥርዓት ያላቸው በመሆናቸው በመካከላቸው ሰላማዊ ግንኙነት ዳብሮ አብሮነት እንዲጠናከር የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚቀመጡበት መድረክ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኃይልን ተጠቅሞ አሉታዊ በሆነ መንገድ የሚመጣ ሰላም ዘላቂ ስለማይሆን ዜጎች በሰላማዊ መንገድ በንግግር የሚፈቱት እና በጋራ መግባባት ላይ መሠረት አድረጎ የሚቀመጥ የመፍትሔ አቅጣጫ ሕዝባዊ መሠረት እንደሚኖረው እና ዘላቂ ሰላምን እንደሚያመጣ በመግለጽ ለዚህ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ዑስታዝ በድሩ ሁሴን “ለቀጣይ ትውልድ የግጭት ታሪክ እንዳናወርስ ያለውን ቁርሾ አስወግደን፣ ሕዝቡን የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማኅበራዊ ተቋማትን ገንብተን፣ የማኅበረሰቦቹን የወንድማማችነት እና አብሮነት ታሪክ ወደ ላቀ ደረጃ አሳድገን ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር በትብብር መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል”፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ሁለቱንም ወንድማማች ሕዝቦች የሚያቀራርቡ፣ አብሮነትን የሚያጠናክሩ እና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ የሚደረስበት መሆኑ ተገልጿል፡፡