የአፋርና የሱማሌ የጋራ የሰላምና የልማት ፎረም ቀጥይ ሊሰራቸው ባቀዳቸው ተግባራት ላይ ውይይት አካሄደ
የአፋርና የሱማሌ የጋራ የሰላምና የልማት ፎረም ቀጥይ ሊሰራቸው ባቀዳቸው ተግባራት ላይ ውይይት አካሄደ
ከግንቦት 6 -7/2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች መካከል ተከስቶ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና ልማትን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የአፋርና የሱማሌ ክልል የጋራ የሰላምና የልማት ፎረም ቀጣይ ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ሥራዎች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዱኛ በቀለ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የሰላም ሚኒስቴር ከሁለቱም ክልሎች ጋር በጋራ በመሆን ተከታታይ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው በተሰራው ስራ እንፃራዊ ሰላም መገኘቱንና ግጭት ተፈጥሮ የነበረባቸውን አካባቢዎች ወደ ልማት ለመቀየር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
አክለውም የሰላም ሚኒስቴር በሁለቱ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት ማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የግጭት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይርጋለም መንግስቱ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የሰላም ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፀጥታ ተቋማት እና ከአፋርና የሱማሌ ክልሎች ጋር በሰራው ከፍተኛ የቅንጅት ስራ በሁለቱም ክልሎች መካከል አንፃራዊ ሰላም መታየቱን ገልፀው እስካሁን ባለው ሂደት በአፋርና ሱማሌ አዋሰኝ አካባቢዎች ያሉ የጝጭት ቀጠናዎች ተለይተዋል፣ ውጤታማ የአመራር ለአመራር ግንኙነት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
አቶ ይርጋለም አክለውም የተቋቋመው የሰላምና የልማት ፎረም ቀጣይ ስራው የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በማሳለጥ ዕርቀ ሰላም ማውረድ፣በሁለቱም ክልሎች መካካል ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እና መተማመን መፍጠር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለዘመናት የቆየውን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት በመጠቀም ችግሮችን በዘላቂነት መፍታትም ሌላው የፎረሙ ሃላፊነት ነው ያሉት አቶ ይርጋለም በቀጣይ በአፋርና በሱማሌ ክልል ህዝቦች መካከል የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንሶች ይካሄዳሉ ብለዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከአፋርና ሱማሌ ክልሎች የተወጣጡ የሰላምና የልማት ፎረም አባላት፣ ከሰላምና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡