የሶማሌና የአፋር ህዝቦች በጋራ የመበልጸግ አቅም ያላቸው ናቸው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የሶማሌና የአፋር ህዝቦች በወንድማማችነት ታሪክ የተሳሰሩና በጋራ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ አቅም ያላቸው ናቸው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

የሶማሌና የአፋር ክልሎች ህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የመድረኩ ቅድመ ምክክርም ከክልሎቹ የተውጣጡ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በቅድመ ምክክር መድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ህዝቦች የጋራ ታሪክ ያላቸው ለብዙ ዘመናትም በፍቅርና አብሮነት የተሻገሩ ናቸው።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በሚቀጥሉት ቀናት የሚካሄደው የወንድማማችነት መድረክ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መፍትሔ በመስጠት መግባባትንና የጋራ ልማትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የክልሎቹ ህዝቦች በጋራ በመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ አቅም ያላቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ከሶማሌ ክልል የመጡት ሻርማርኬ መሀሙድ፥ የክልሎቹ መንግስታት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የወሰዱት ቁርጠኝነት ለህዝቡ ትልቅ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።

ከአፋር ክልል የመጡት መሀመድ ዑስማን(ዶ/ር)፥ ውይይቱ የአፋርና ሶማሌ ክልል ህዝቦችን ግንኙነት በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የሶማሌና የአፋር ክልል ህዝቦች የማይነጣጠል የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳላቸው በማንሳት፤ መድረኩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለመጪው ትውልድ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ለማውረስ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ከሶማሌ ክልል የመጡት ሂቦ አህመድ እንደሚሉት፥ የአፋርና ሶማሌ ህዝቦች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ናቸው።

 

የሰላም ሚኒስቴርና የክልሎቹ መንግስታት የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ የወሰዱት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሁለቱ ህዝቦች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በባህላዊ መንገድ በምክክር የመፍታት የካበተ ልምድ እንዳላቸው የጠቀሱት ደግሞ ከአፋር ክልል የመጡት ሀዋ አሊ ናቸው።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዲሁም የሁለቱ ክልሎች የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በጅግጅጋና በሰመራ ከተሞች የህዝቦችን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል የኢፍጣር መርሃ ግብሮች መካሄዳቸው ይታወሳል።

#ኢዜአ