የሰላም ሚኒስቴር በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክከር ቤት ከውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ
የሰላም ሚኒስቴር በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክከር ቤት ከውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ
"ግጭቶችን ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል" ፡- ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር
ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክከር ቤት ከውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ በሁለቱ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት ማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሰላም ሚኒስቴር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአብሮነት የፀናች ሀገርን ለመገንባት ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ክቡር አቶ መሐመድ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን መንስኤዎች በማጥናት ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ዲማ ነገዎ የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት በቦታው በመገኘት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን ግጭት ያለበትን ደረጃ ምልከታ ማድረጉን ገልፀው ግጭቱን በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊነት ኮሚቴው ተገንዝቧል ብለዋል፡፡ በዚህ መድረክም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት እንደመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለባቸውን ኃላፊነት በመረዳት ወደ ቀጣይ ስራዎች ለመሻገር ያግዛል በማለት ገልፀዋል፡፡
የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩጌታ ገነነ በአፋርና በሶማሌ ክልል የተከሰተው ግጭት የቅርብ ጊዜ እንዳልሆነ አንስተው የቆየ ከመሆኑ የተነሳ እያደገ መጥቷል ብለዋል። ክቡር አቶ ቸሩጌታ አያይዘውም እንደዚህ የቆዩና ስር የሰደዱ ግጭቶች ሀገርን የሚጎዱ በመሆናቸው የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ክትትል እንዲያደርግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘቷል ብለዋል ፡፡ በተደጋጋሚ የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቶ አሁን ላይ በክልሎች መካከል ያለው መቀራረብ ተሻሽሏል በማለት ገልፀዋል፡፡
በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርት በሰላም ሚኒስቴር የግጭት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ በሆኑት አቶ ይርጋለም መንግስቱ ቀርቧል፡፡
በሁለቱ ክልሎች የሚከሰቱ የግጭቶች መሠረታዊ መነሻ በአብዛኛው የተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ፣ የእንስሳት ዝርፊያና መበቃቀል እንደሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በክልል አመራሮች መካከል መግባባት ላይ የተደረሰ በመሆኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል እየታየ ያለውን መቀራረብ ለማጠናከር በቀጣይ ተከታታይነት ያላቸው የማህበረሰብ ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል ፣ ለግጭቶች መነሳት እንደመንስኤ ከተገለጹት ውጭ አለፍ ብሎ በማሰብ ሌሎች ችግሮችንም መፈተሽ እንደሚያስፈልግ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመው የሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተዘጋጀው እቅድ እንዲሳካ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል በማለት አንስተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢፌዲሪ የህ/ተ/ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ፣ የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተገኝተዋል።