በብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ በተካሄደው ጥናት ውጤት ውይይት ተካሄደ
በብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ በተካሄደው ጥናት ውጤት ውይይት ተካሄደ
ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከባህርዳር ኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ ባካሄደው ጥናት ውጤት ውይይት አካሄደ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ እንደተናገሩት በብሔራዊ በጎፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ላይ የተካሄደው ጥናት ዓላማ እስካሁን የተካሔደው የበጎፈቃድ ስራዎችን ውጤታማ መሆኑንና ምን አይነት ክፍተት እና ውስንነቶች እንዳሉ በመለየት ያገኘናቸውን ውጤቶች ለማስቀጠል የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም በወጣቱ ዘንድ በጎ ፈቃደኝነት ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እና በቅብብሎሽ የሚተላለፍ እንዲሆን በጥናት መደገፍ ያስፈልጋል በማለት ገልፀዋል፡፡
የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በሀገራችን ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ወጣት በመሆኑ የብሔራዊ በጎፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም የተፈለገበት ዋና ምክንያት ወጣቱ እርስ በእርስ በሚገባ በመተዋወቅ ሀገር ወዳድ ሆኖ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ሀገር ወዳድ ዜጋን ለማፍራት የሚያስችል ፕሮግራም እንዲሆንና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በተሰሩ ሥራዎችንና በአስራ ሁለት ዙር በተሰጡ ስልጠናዎች ስምሪትን ጨምሮ የታዩ ጉድለቶችን በመለየት የፕሮግራሙ ውጤታማነትን ለማስቀጠል እንደዚህ አይነት ጥናቶች ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደመቀ ላቀው ጥናቱን አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ጥናቱ ሁለት ዓመት የፈጀና አብዛኞችን ክልሎች እና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ያካተተ ነው ያሉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ተቀዳሚ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው ጥናቱን ከተለያዩ የትምህርት መስኮች የተውጣጡ ምሁራን ያጠኑት ሲሆን በጥናቱም ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ሰፊ ግብዓቶች የተገኙበ ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ የበጎፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚያግዙ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ፀንተው የቆዩ እሴቶችን ለመጠበቅ የሚረዱ ውጤቶች የተገኙበት እንዲሁም ለሰላም ግንባታ እና ሀገራዊ አንድነት ትልቅ አስተዋፆ እንዳበረከተ የጥናቱ ውጤት ያመላክታል ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡