ፌዴራሊዝም እና የፌዴራል ሥርዓት
ፌዴራሊዝም እና የፌዴራል ሥርዓት
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣን እና ተግባራት መካከከል በመንግስታት መካከል ያሉትን ግንኙነቶች በመከታተል ክፍተቶችና ችግሮች ለይቶ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ በአሰራር ማዕቀፎችና ፕሮሲጀሮች በማጠናከር እንዲሁም ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመስማማቶችን (ግጭቶችን) በድርድር፣በመተባበበር እና በአጋርነት እንዲፈቱ በማስወገድ ወይም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዳበረና ቀጣይነት ያለው የፌደራል ስርአትና የተጠናከረ የመንግስታት ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ የጋራ የሆነ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ያስችላል፡፡
የፌደራሊዝም እና መንግስታት ግንኙነት መነሻ የፌደራል ስርአቱን አሰመልክቶ ከፌዴራል መንግስት የሚተላለፍ ትዕዛዝና ጥያቄ፣ ከክልሎች የሚቀርብ ጥያቄ እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስታት ግንኙነት ፎረሞችና የምርምር ውጤቶች የተገኙ መረጃዎችና የተለዩ ችግሮችና ክፍተቶች ሊሆን ይችላል፡፡ መድረሻውም እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተውና ክፍተቶቹና ችግሮቹም ተቀርፈው የተመሰረተ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የፌደራል ስርአት እና መንግስታት ግንኙነት ተግባራዊ ማድረግ ይሆናል፡፡
ፌዴራሊዝም የፌዴራል ሥርዓት ታካዊ ዳራ
በዓለማችን ዘመናዊነት እየተስፋፋ፣ የመረጃ ልውውጥ እያደገና የዴሞክራሲ ባህል እየጎለበተ ሲሄድና ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት ዝውውር እየጨመረ በመምጣቱ ብዝሃነት የበርካታ ሃገራት መገለጫ እየሆነ መጣ፡፡ ስለሆነም ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል ስርዓት የመገንባት ጉዳይ ችላ የማይባል ጉዳይ ሆነ፡፡ በተለይ የማንነትና የእኩልነት ጉዳይ የፖለቲካ ጥያቄ በሆነበት ሀገር ጥያቄውን በፍትሃዊነት ማስተናገድ ትልቅ ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማንነትና በቋንቋ የመጠቀም መብት፣ የራስ አስተዳዳርን የማቋቋም ፍላጎት፣ ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍልና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከሀገር ሀገር እየተስፋፉ በመሄዳቸው መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮች ሆነዋል፡፡
የብዝሃነት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሀገራት የተለያየ የመፍትሄ መንገዶችን ተከትለዋል፡፡ የተወሰኑት ሀገራት ብዝሃነትን የማስተናገድ ጉዳይ በትኩረት በመያዝ በሥርዓት ለመመለስ ሲሞክሩ ሌሎቹ ደግሞ ከፖለቲካው አውድ ለማጥፋት የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ በእነዚህ ሙከራዎች የተሳካላቸው ጥቂት ሀገራት ቢኖሩም፤ ለማያባራ ጦርነትና ደም መፋሰስ የተዳረጉም ቀላል አይደሉም፡፡
ሀገራት ከብዝሃነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተጠቀሟቸው ስልቶች አንዱ (ብዝሃነትን) ከፖለቲካው ምህዳር ማስወገድ ነው፡፡ ከነዚህም መንገዶች፡- የመዋጥ (Assimilation)፣ የማዋሃድ (Integration) እና አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ቡድኖች (ብሔረሰቦች) የተወሰነ መብት መስጠት (Minority Rights) ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ብዝሃነትን በፍትሃዊነት ለማስተናገድ የሞከሩ ሀገራት የተከተሏቸው መንገዶች የመግባባት ዴሞክራሲ (Consocationalism)፣ ፌዴራሊዝም እና የሁለቱ ሥርዓቶች ጥምር ናቸው፡፡ በዚህም በአጭሩ የምናየው ብዝሃነትን ለማስተናገድ በብዙ ሀገራት ተመራጭ የሆነውን የፌዴራል ሥርዓትን ይሆናል፡፡
ፌደራሊዝም ረጅም መንገድ የተጓዘ የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ እንደ ፌደራሊዝም ምሁሩ ዳንኤል ኤላዛር ከሆነ የፌደራዝም ታሪካዊ አመጣጥን በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ይሄውም የመጀመሪያው በመፅሀፍ ቅዱስ የተጠቀሰው የእስራኤላውያን የጎሳ አወቃቀር ሲሆን ይሄውም የተለያዩ የእስራኤል ጎሳዎች ባልተማከለ የፌደራል አወቃቀር ሥር ይተዳደሩ እንደነበር ይጠቅሳል (Elazar, 1987)፡፡ ይህም ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት እነዚህ ጎሣዎች የፌደራል ሥርዓትን በመመስረት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ያመለክታል፡፡ ምንም እንኳን የውጭ ጫና ፌደሬሽኑን ያፈረሰው ቢሆንም አይሁዳውያን የመጀመሪያውን ፌዴሬሽን እንዳቋቋሙ ይታመናል፡፡ በሁለተኛ የሚጠቀሰው ደግሞ ከዛሬ 700 ዓመት በፊት እንደተመሰረተ የሚታመነው የስዊስ ኮንፌደሬሽን ነው፡፡ ይህም የፕሮቴስታንት ተሃድሶን (Protestant Reformation) በማፋጠን ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ነፃ ህዝቦችን እንደፈጠረ ይታመናል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከአሜሪካ ፌደራሊዝም ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከዛሬ ሁለት መቶ አመት በፊት የተቋቋመው የአሜሪካ ፌደራሊዝም የመጀመሪያው ዘመናዊ የፌደራል ሥርዓት በመባል ይታወቃል (Elazar, 1987)፡፡ ይህ የመንግስት አወቃቀር በአሁኑ ሰዓት ልዕለ ሃያል የፌደራል ሀገር የሆነችውን አሜሪካንን ያቋቋመ ነው፡፡ ይህም ነፃነትን እና ፌደራሊዝምን አንድ ላይ በማጣመር የአህጉር መጠን ያላትን አሜሪካ በአንድ መንግስት ጥላ ሥር እንድትሆን አስችሏታል፡፡
ባለፉት 200 ዓመታት ውስጥ ያለውን የፌደራሊዝም አመጣጥና እድገትን ስንመለከት ደግሞ ታዋቂው የፌደራሊዝም ምሁር ጆርጅ አንደርሰን አራት ታሪካዊ የፌደራሊዝም ማዕበሎች (Historical Waves) እንደነበሩ ያስረዳል (Anderson, 2008)፡፡ የመጀመሪያው የታሪክ ማዕበል ከ18ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ እስከ 19ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ የነበረው ሲሆን በዚህ ወቅት ቀድሞ ነፃ የነበሩ ትናንሽ ሀገሮች ወደ አንድ በመምጣት አዳዲስ የፌደራል ሀገራትን የፈጠሩበት ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ የስዊስና የአሜሪካን ኮንፈደሬሽን የተቋቋሙት በዚህ ወቅት ነበር፡፡
የአሜሪካን የኮንፊደሬሽን ተሞክሮ የቆየው እንደ ጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1781 እስከ 1789 ለዘጠኝ ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ በ1789 ግን 13 የሚሆኑ ግዛቶች ወደ አንድ በመምጣት ዘመናዊውን የአሜሪካ ፌዴራሊዝም መፍጠር ችለዋል፡፡ የስዊስ ኮንፌደሬሽን ደግሞ ለሦስት ዓመታት በካቶሊክና በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መካከል ተካሂዶ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በ1848 የተቋቋመ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በ1871 የተቋቋመው የጀርመን የፌደራል ህገ-መንግስት ነበር፡፡ ይህ የመንግስት አወቃቀር ልል የሆነ የኮንፈደሬሽን አወቃቀር እንደነበር ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌለኛው ደግሞ ሦስት የእንግሊዝ ሰሜን አሜሪካ ቅኝ ተገዥዎች በጋራ በመጣመር ያቋቋሙትና በ1867 የተቋቋመው የካናዳ ኮንፈደሬሽን ተጠቃሽ ነው፡፡ የአውስትራሊያ ፌዴሬሽን ደግሞ ስድስት ቅኝ ተገዥ የነበሩ ግዛቶችን ወደ አንድ በማምጣት በ1901 የተቋቋመ ነው፡፡ በላቲን አሜሪካ/ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ደግሞ እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ የመሳሰሉት ፌደሬሽኖች የተቋቋሙት በዚሁ ወቅት ነበር፡፡
ሁለተኛው ማዕበል የሚባለው ደግሞ የቅኝ ግዛት መፍረስን ተከትሎ የተቋቋሙ የፌደራል ሀገራትን ይመለከታል፡፡ በዚህ ወቅት ከተቋቋሙት የፌደራል ሀገሮች ውስጥ የተሳካላቸው ቢኖሩም የተወሰኑት በመበታተን የተለያዩ ሀገራት ለመሆን በቅተዋል፡፡ የተሳካላቸው ወይም ከቅኝ ግዛት በኋላ እንደ ፌደራል ሀገር ከተቋቋሙት ውስጥ የግዛት አንድነታቸውን ጠብቀው ከቆዩት ውስጥ ህንድ፣ ፓኪስታን እና ናይጀሪያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ህንድ እና ፓኪስታን የ1847 ክፍፍልን ተከትሎ በፌደራል አወቃቀር ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ ሀገራት ናቸው፡፡ ሌሎች እንደ ዌስት ኢንድስ፣ መካከለኛው አፍሪካ ፌደሬሽን፣ የማሊ ፌደሬሽን እና የዩጋንዳ ፌደሬሽን የመሳሰሉት ግን ውጤታማ ካልነበሩት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የኮሚኒዝም መፈራረስን ተከትሎ የተቋቋሙ የፌደራል ሀገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህልም የራሽያ ፌደሬሽን የሶቭየት ህብረት መፍረስን ተከትሎ የተቋቋመ ሲሆን ቦስኒያ ሄርዞጎቪና ደግሞ የዩጎዝላቪያ ፌዴሬሽን መፍረስን ተከትሎ የተቋቋሙ የፌደራል ሃገራት ናቸው፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ደግሞ ቀድሞ የተማከለ አስተዳደር ይከተሉ ከነበሩት ሃገራት ወደ ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር የቀየሩ ይጎበኙታል፡፡ ለምሳሌ ያህልም እንደ ቤልጀም፣ ስፔን፣ ደቡብ አፍሪካ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ሌሎች ደግሞ በየሀገሮቻቸው ውስጥ የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭት ተከትሎ የተቋቋሙ ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኮንጎ እና ኢራቅን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይቀጥላል