ለሀገራዊ አዎንታዊ ሰላም ግንባታ እና ብሄራዊ ጥቅም መረጋገጥ የግል ሚዲያዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የካቲት 26/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከንግድ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ምክክር አደረጉ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በመድረኩ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር “በዜጎች መካከል አብሮነት እና አንድነት እንዲጠናከር፤ አመለካከትና አስተሳሰብን የሚያቃና መረጃ ተደራሽ በማድረግ የሁላችንም የሆነችው ሀገራችን ወደ ፊት እንድትራመድ ተገቢውን ሚና መጫወት ይገባል”፤ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ ኅብረተሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን እና በአብሮነት እንዲቆም ማገዝ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን ገልፀው የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ለዚህ ሀገራዊ ዓላማ ተገቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ሚዲያ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው “ሚዲያ ለሀገር ግንባታም ሆነ ለግጭቶች መባባስ የጎላ ሚና ስለሚኖራቸው በሰላም እና በሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል”፤ ብለዋል።

የመድረኩ ተሳተፊዎች ባነሷቸው ሐሳቦች የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ መሥራት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው የማኅበረሰብ እሴቶችን ለሚያዳብሩና አዎንታዊ አመለካከቶችን ለሚገነቡ ጥረቶች ቅድሚያ መስጠት፤ ሥነ ምግባራዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። የንግድ መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች እንዲጠናከሩ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስቴር የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት እና የሚዲያ ተቋማት ሚና በሀገር ግንባታ በሚል ርዕስ አቶ ሀለፎም አባይ በሰላም ሚኒስቴር የሀገር ግንባታ ተወካይ መሪ ሥራ አስፈፃሚ፣ በሰላም ግንባታ የንግድ መገናኛ ብዙኃን ሚናቸውን ከመወጣት ረገድ የሚገኙበት ሁኔታን አስመልክቶ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የንግድ መገናኛ ብዙኃን ክትትል ዴስክ ኃላፊ በሆኑት አቶ አብዩ መኮንን እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ አንተነህ ተስፋዬ (ዶ/ር) ደግሞ በሰላም ግንባታ የንግድ መገናኛ ብዙኃን ሚና በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ሀገራዊ ጥቅሞችን በውል መገንዘብ እንደሚየስፈልግ፣ በሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የግንኙነት አግባብ መፍጠር፣ የዕውቅና አሰጣጥ አግባቦችን ማዘጋጀት፣ የጋራ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡