በጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረን አብሮነትና ወንድማማችነትን እናጠናክራለን - የአፋርና የሶማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
በጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረን አብሮነትና ወንድማማችነትን እናጠናክራለን - የአፋርና የሶማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
በጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረን አብሮነትና ወንድማማችነትን እናጠናክራለን ሲሉ የአፋርና የሶማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።
የአፋርና የሶማሌ ክልል ህዝቦች አብሮነትን ማጠናከር ያለመ የጋራ ኢፍጣር መርሃ ግብር የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የተጀመረው የአብሮነትና የወንድማማችነት መንገድ ይጠናከራል ብለዋል።
የሁለቱን ክልል ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት የበለጠ የሚያጠናክሩ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረው በቀጣይ የጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለዘላቂ ሰላም እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በርካታ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሁለቱን ህዝቦች ትስስር የበለጠ የሚያጠናክሩ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪሰ፣ ሁለቱ ክልሎች ተቀራርበው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች በርካታ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተው ይህን ለማጠናከርና ወንድማማችነትን ለማጉላት የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እሰልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ በተያዘው ረመዳን ወር በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እየተጉ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።