በአገር አቀፍ ደረጃ ''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል  መሪ ሃሳብ  የሰላም የሩጫ ውድድር  ሊካሄድ ነው

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ሰኔ 1/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች  እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል  መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄደውን  የሰላም ሩጫ አስመልክቶ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሐ  ግብሩ ላይ  ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስቴር ሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ  የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ዜጎች በዘላቂ ሰላምና በብሔራዊ መግባባት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ሰፋፊ የንቅናቄ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል  መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሰላም  የሩጫ ውድድር የዚህ አንዱ አካል ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው ከስፖርት የበለጠ የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት ማሳያ የለም ብለዋል።

ክቡር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ አክለውም ሩጫ የኢትዮጵያ  የአሸናፊነት መንፈስ ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን ይህን የአሸናፊነት መንፈስ ለሰላም ማዋል ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን ሁላችንም ሰላም መሆንን እንፈልጋለን የምንፈልገውን ሰላም ደግሞ የምናሰፍነው ሁላችንም ተግተን ስንሰራ ነው ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር  የሰላም ሩጫ ውድድር ሲያዘጋጅ  ከስፖርታዊነት ውድድር ባሻገር ዜጎች ዕርስ በዕርስ እንዲተዋወቁ ፣ የአንድነት መንፈስ እንዲያጎለብቱ  እና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በማሰብ ነው ብለዋል።

ስለ ሰላም ሩጫ ውድድሩ አጠቃላይ መርሃ ግብር አጭር ማብራሪያ የሰጡት የሰላም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ እና የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አዱኛ በቀለ የሰላም ሩጫ ውድድሩ ዓላማ በሀገራችን እየተገኘ ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ዜጎች በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽፆ እንዲያበረክቱ ለማስቻል እና  በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትን መቀራረብን እንዲሁም መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት መሆኑን ገልፀዋል።

ሩጫው ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ዋና ዋና ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን የሚሸፍነው ርዝመት በአዲስ አበባ 6 ኪ.ሜ ሲሆን መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ ሆኖ ሌሎች እንደ አካባቢው ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል ተብሏል።