አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ
አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ
ግንቦት 9/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ከህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ጋር በመተባበር የአምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የመንግሥት ግንኙነት፣የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገመንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ የተከበሩ ወ/ሮ ባንቺይርጋ መለሠ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አደረጃጀት የምትከተል ሀገር እንደመሆኗ መጠን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያስችሉ መደበኛ የመንግስታት ግንኙነቶች መኖር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገመንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ኢ/ር ሙሃመድ ሻሌ በበኩላቸው ይህ መድረኩ የአራቱ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች (ሱማሌ፣አፋር፣ሐረር፣ኦሮሚያ) እና የድሬዳዋ አስተዳደር መካከል የዕርስ በዕርስ የመንግስታት ግንኙነት ስርዓትን ለማጠናከር የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ይህ የግንኙነት አግባብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ለማጎልበት፣ የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሪክተር ዶ/ር ኃይለየሱስ ታዬ ''ውጤታማ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከር አስፈላጊነት'' በሚል ርዕስ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ''ውጤታማ የተጎራባች ክልሎች የግንኙነት ስርዓት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከር አስፈላጊነት'' የሚል ርዕስ ደግሞ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ ትግሉ መለሰ በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
መድረኩን ያጠቃለሉት በሚኒስትር ዴዔታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የዕርስ በዕርስ የመንግስታት ግንኙነት ፎረም በክልሎች መካከል ያለውን የዕርስ በዕርስ ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር በተናጠል የሚደረጉ የሰላም ሥራዎችን በአንድነት እና በተባበረ መንፈስ በመስራት ያሉብንን የውስጥ ችግሮች ለመፍታት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ስርዓት ያለ መንግስታት ግንኙነት ጠንካራ ሆኖ መቆም አይችልም ያሉት የተከበሩ አቶ ካይዳኪ የክልሎች የዕርስ በዕርስ የመንግስታት ግንኙነት ፎረም መመስረት የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳዮችን በጋራ ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፣የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል፣ የአራቱ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች(ሱማሌ፣አፋር፣ሐረር፣ኦሮሚያ) እና የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።