ሀገር አቀፍ ‘ወጣቶች ለሰላም’ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሄደ
ሀገር አቀፍ ‘ወጣቶች ለሰላም’ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሄደ
ሰኔ 29/2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣የሰላም ሚኒስቴር ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር በመሆን "ሀገሬን እገነባለሁ፣ ኃላፊነቴን እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እያካሄደ የቆየው ወጣቶች ለሰላም ሀገራዊ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የሀገራዊ ንቅናቄው ዓላማ ወጣቶች ብሔራዊ ትርክትን በመገንባት ዘላቂ ሰላምን መርህ የሚያደርጉበት፣ ለአብሮነትና ሀገራዊ አንድነት ተግባቦት መፍጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ንቅናቄው ሀገራዊ ራዕያችንን መሠረት በማድረግ ያሉንን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ተግዳሮቶችን ለመሻገር እና ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ እየተተገበሩ ያሉትን ሁሉን አቀፍ ተግባራት ወጣቶች እንዲረዱ ግንዛቤ ያዳበሩበት ንቅናቄ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ወጣቱ የፈጠራ አቅሙን የሚያዳብርበት ፕሮጀክቶች በስፋት መቀረጻቸውንም አመላክተው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር የጀመረችውን ጥረት ስኬታማነት ወጣቱ በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርግ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ባሰሙት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት “ወጣቶች ዛሬ ላይ ሆነው፤ ነገ የሚመሯትን ሀገር በራሳቸው እጅ መገንባት የሚችሉ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍል ናቸው። ለሀገር ግንባታና ሰላም መስፈን የሚመነዘር ብርቱ ጉልበት ያላቸው፤ የእምቅ ኃይል ባለቤት በመሆናቸው አንዲት ሀገር በምን ያህል ደረጃ ራሷን መተካትና ማስቀጠል ስለመቻሏ ጥሩ ማሳያ ናቸው” በማለት ሀገራችን ያስመዘገበቻቸው ለውጦች በዋነኛነት በወጣቶች ተሳትፎና መስዋዕትነት የመጡ ስለመሆኑ እና በታሪክ ውስጥ ወጣቶች ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ እና ለሀገራዊ ዕድገት በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ሆነው በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ውስጥ የጎላ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ “ላለፉት ሁለት ወራት ከቀበሌ ጀምሮ የተደረገው የወጣቶች ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩትን በጎ ሁኔታዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ክፍተቶችን ደግሞ በጋራ በትብብርና በምክክር ለመሙላት ወጣቱ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰበት ነው” በማለት ሀገራችን ፀንታ እንድትቆምና ፈተናዎችን እንድትሻገር የሚያስችል ተግባቦት የተፈጠረበት መሆኑን ገልፀዋል።

ወጣቶች የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ሀገራዊ መተባበርን ማጠናከር፣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የሀገራችን ብልፅና እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡