በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ሰልጣኞች የምርቃት ስነ-ስርዓት ተካሄደ
በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ሰልጣኞች የምርቃት ስነ-ስርዓት ተካሄደ
መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ከወራቤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በ12ኛው ዙር መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰአገልግሎት ወጣቶችን በወራቤ ዩኒቨርስቲ አስመርቋል።
በፕሮግራሙ ተገኝተው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሀገራችንን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት ከሄድንባችው መንገዶች መካከል የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ 11 ዙሮች በጎ ፈቃደኞችን በማሰልጠን በመላው ሀገርቱ ስምሪት በመስጠት ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦቿ የተሳሰሩና የተጋመዱ በመሆናቸው መነጠል አለመቻላችን አንድነታችንን ለማይወዱ ችግር ሆኖባቸዋል። ይህ አንድነታችን ደግሞ በይበልጥ እንዲጎለብት የበለጠ ልንተጋ ይገባል ብለዋል።
ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ እንፃራዊ ሰላም ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም ያሉብንን ችግሮች እርስ በርሳችን እየተነጋገርን የምንፈታው ችግር እንጂ ሌሎች እንደሚያወርዱት ሙሾ አይደለም ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ችግሮች በተመሳሳይ ሰዓት መጥተው ሁሉንም ችግሮች በተመሳሳይ ሰዓት መመከት የቻልን ድንቅ የአድዋ ልጆች ነን፤ ይህንንም በወሰዳችኋቸው ስልጠናዎች ውስጥ በብዙ ተገንዝባችኋል ብዬ አስባለሁ ብለው አሁን ያለንበት ጊዜ ዘመኑን የዋጀ አርበኝት የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበንና ይህንን አስጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የዛሬ ተመራቂዎች ቁልፍ ተልዕኮ እንደወሰድችሁ ተስፋ አደርጋለሁም ብለዋል።
አያይዘውም የሰላም ሥራ የአንድ ወገን ባለመሆኑ ፤ የህዝባችንን የተለያየ ቋንቋ ማወቅ በማንኛውም የስራ መስክ ስንሰማራ ተመራጭነታችንን የሚያሰፋ ከመሆኑም በላይ የራሳችንን አቅም መገንባት እንድንችል የሚያደርገን፣ እንዲሁም አንዳችን በሌላችን ልብ ውስጥ በቀላሉ እንድንገባ ዕድል የሚፈጥርልን ነውና ተያይዘን የሀገርና የሰላም ባለቤት ሆነን መስራት እንዳለብን አሳስበዋል።
በመጨረሻም ለሰልጣኞች መልካም የአገልግሎት ጊዜ እንዲሆን ተመኝተው ለዚህ ስልጠና መሳካት የማይተካ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ቶፊቅ ጀማል (ዶ/ር) በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ ቃል በሀገር ግንባታና ዘላቂ ልማት ላይ በትጋትና በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንድታገለግሉ ኢትዮጵያ በብዙ ትጠብቃለች ያሉ ሲሆን፤ በጎ ፈቃደኝነት የመልካም ስብዕና ባለቤት መሆን በመሆኑ፤ ባደረጋችሁት የባህል ልውውጥ እርስ በርስ መተዋወቃችሁ ለአገልግሎት በምትሄዱበት ቦታ ሁሉ በትጋትና በታማኝነት አገልግሎታችሁን ለመፈጸም ያስችላችኋል ብለዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከክልል ተጋባዥ እንግዶችና እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።