ከችግር ተንታኝ አስተሳሰብ ተላቆ ሀገር የሚያውቅና ሀገር የሚያከብር ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
ከችግር ተንታኝ አስተሳሰብ ተላቆ ሀገር የሚያውቅና ሀገር የሚያከብር ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በሰላም ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት "ብሔራዊ ጥቅሞችቻችንና ቀጠናዊ ትስስራችን ለሚዛናዊ የህዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከዩኒቨርሲቲው መስመራዊ መኮንኖችና ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
ውይይቱን ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርጋዴየር ጀኔራል ከበደ ረጋሳ ሁሉም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ቀጠናዊ ትስስራችን ላይ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት የሚችል ሃሳብ በማዋጣት የጋራ ግንዛቤ ፈጥሮ እንደ ሰራዊት መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል ።
የሀገራት ቀጠናዊ ትስስር የሚጠናከረው የጋራ ሰላምን በማስፈን ፣ የኢኮኖሚ ውህደት በመፈጠር እና የጅኦ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተለዋዋጭነትን ጠንቅቆ በመረዳት ውስጣዊና ውጫዊ ግጭቶች የሚፈጥሩ የጥፋት ሃይሎችን በንቃት መቆጣጠር ላይ በማተኮር መሆኑንም ጀኔራል መኮንኑ አስረድተዋል ፡፡
እንደ ሀገር ሰላምና ልማትን አጠናክሮ በመቀጠል የነገን ትውልድ መጥቀም የሚችሉ መሰረታዊና አስፈላጊ ተቋማትን እየገነቡ መቀጠል እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ ውይይቱን የመሩት በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና አሲስታንት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ ናቸው ።
ሀገር ቀጣይነት ያለው የትውልዶሽ ቅብብል ውጤት ናት ያሉት ዶክተር ሮባ ትውልዱ በህብረ ብሔራዊነቱ ደምቆና ኮርቶ ልዩነትን በፍቅር እያጣጣመ የሚቀጥል እንጂ እያጣመመ መሄድ እንደሌለበትም አብራርተዋል ።
እንደ ሀገር ሰላምና ልማትን አጠናክሮ በመቀጠል የነገን ትውልድ መጥቀም የሚችሉ የትምህርትና የልማት ተቋማትን በውጤት እየገነቡ መቀጠል እንደሚያስፈልግ የህግ መምህሩ በስፋት ገልፀዋል ።
በውይይቱ ላይ ሰፊ ማጠቃለያ የሰጡት ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ኃላፊ አቶ ገዛሃኝ ጥላሁን ሁሉም ከችግር ተንታኝ አስተሳሰብ ተላቆ ሀገር የሚያውቅና ሀገር የሚያከብር ትውልድ በውል ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል ።
ውይይቱ እንደ ትምህርት ተቋም ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች የአገርን ሉዓላዊነት ማጠናከር የሚችሉ እሴቶችን በማጎልበት አሁናዊና አለማቀፋዊ ዝርዝር ሁኔታዎች
ላይ ሠፊ ግንዛቤ መፍጠር እንዲችል ሰላም ሚኒስቴር እስከ ማህበረሰብ ድረስ ወርዶ መሰራት እንዳለበትም ተጠቁሟል ።
ምንጭ ፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ