በብሔራዊ ጥቅሞችና ቀጣናዊ ትስስር ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረክ ተካሄደ
በብሔራዊ ጥቅሞችና ቀጣናዊ ትስስር ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረክ ተካሄደ
ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የህዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል ርዕስ ውይይት አካሂዷል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እንደተናገሩት እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ሰዓት ሰላምን እጅግ እንደሚፈልግ ተናግረዋል :: ሀገር ብዙ ኢንቨስት አድርጋ ያስተማረችው ምሁር ስለ ሃገሩ ዕጣ ፈንታና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር መሄድ ያለብን በምን አቅጣጫ እንደሆነ ወሳኝ ምክረሃሳብ ማቅረብ መብት ሳይሆን ብሔራዊ ግዴታው ነው ብለዋል::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዳኘ ሽብሩ (ዶ/ር )ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል::
የዕለቱ የክብር እንግዳ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ጅሀድ ናስር የውይይት መድረኩ ዓላማ የአንድ ቀን ምክክር ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ሰላምን ለመገንባትና የህዝቦችን ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል፣ መንግስትም ሆነ በተቃራኒው ጎራ ያሉ አካላት የሀገርን አንድነት ለማጠናከርና ለቀጣናው ፖለቲካ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ብሎም ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅሞች የምታስከብርና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ለማስቻል ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ምሁራን በእውቀት የተደገፈ ሃሳብና አቅጣጫ እንዲያመላክቱ ይፈለጋል ብለዋል::
በሰላም ሚኒስቴር በሀገር ግንባታ ዘርፍ የብሄራዊ መግባባት ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ሲሳይ ብርሌ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሀገር ግንባታ አንፃር ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የተለያዩ የምክክር መድረኮች በማዘጋጀት በመሥራት ላይ እንደሆነ ጠቁመው የዛሬው መድረክም ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦች የተገኙባቸው መሆኑ አንስተዋል::
ምንጭ:- ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ