ለ11ኛ ዙር ለመሰልጠን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የገቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሄደ
ለ11ኛ ዙር ለመሰልጠን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የገቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሄደ
ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር)፣ ለ11ኛ ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ለመሰልጠን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የገቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሂዷል።
ፕሮግራሙ በሐይማኖት አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች ፀሎት እና ምርቃት ተጀምሯል።
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) "በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ ሐሳብ በሰላም ሚኒስቴር የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ በማድረግ ፤ በማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መጠነኛ መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር አወንታዊ ሰላም ከሚገነባባቸው መንገዶች አንዱ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ነው ያሉ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም የሰላም አባሳደሮች ተፈጥረዋል፣ህዝቦች ተቀራርበዋል፣ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ዳብረዋል ብለዋል።
ይህ ፕሮግራም ለግላችን እና ለሀገራችን ህልም መሳካት ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ለመሰልጠን ዛሬ የተገኛችሁ ወጣቶች ድንበር ሳይሆን ድልድይ ሰሪዎች ናችሁ ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በበኩላቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ሲያሰለጥን መቆየታቸውን ገልፀው ዩኒቨርስቲው ይህን ሀገራዊ ተልዕኮ ተቀብሎ ማስተናገዱ ለእኛ ኩራት ነው ብለዋል ።
የሰላም ሚኒስቴር ለ10ኛ ተከታታይ ዙር ባካሄደው የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ከ75 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ በተለያዩ የሀገራችን ክፍል አሰማርቷል።
የሰላም ሚኒስቴር በ11ኛ ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም መርሃ ግብር 1500 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስገብቶ ያሰለጥናል።