የፌዴራሊዝም እና የመንግስታት ግንኙነት
የፌዴራሊዝም እና የመንግስታት ግንኙነት
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣን እና ተግባር መካከል የፌደራሊዝም እና መንግስታት ግንኙነቱን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴር ቤቱ በመንግስታት መካከል (በፌዴራል እና በክልሎች መካከል እንዲሁም በክልል መንግስታት መካከል) ያሉትን ግንኙነቶች በመከታተል ክፍተቶችና ችግሮች ለይቶ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ በአሰራርና ማዕቀፎችን በማጠናከር እንዲሁም ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን (ግጭቶችን) በድርድር፣በመተባበበር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዳበረና ቀጣይነት ያለው የፌደራል ስርአትና የተጠናከረ የመንግስታት ግንኙነት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት ዓላማ የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ ማስጠበቅ፣ ጠንካራ የሕዝቦች ግንኙነትና ትስስር መፍጠር፣ ሃገራዊ እና ክልላዊ ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲፈፀሙ ለማድረግ እንዲሁም በመንግስታት መካከል ያሉ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ በአጋርነት ላይ የተመሰረተ የአመራር መርሆ በማስፈን በጋራ የሚመሩበትና የሚመክሩበት ስርዓት መገንባት ነው።
የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓቱን ለማጠናከርና ቀጣይነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተቋማዊ ስርዓት ለመፍጠር እንደ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
ከዚህ በተጨማሪም በፌዴራል መንግስትና በክልሎች እንዲሁም በክልሎች መካከል እርስ በርስ የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈቱበትን የግንኙነት አግባብ መዘርጋትና ማጠናከ ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
የሰላም ሚኒስቴር በፌደራሊዝም እና መንግስታት ግንኙነት ዙሪያ ለዜጎች፣ ቤተሰቦችና ማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና በፌደራል ስርዓቱ ላይ ሕዝቡ ግንዛቤው እንዲያድግና ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደርስ የሚያስችል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ችግሮች ሲከሰቱ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዳበረና ቀጣይነት ያለው የፌደራል ስርዓትና የተጠናከረ የመንግስታት ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ሌላው የተቋሙ ተግባር ነው።
የሰላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓቱ ሞተር መሆኑን በማመን በፌዴራልና በክልል እንዲሁም በክልሎች መካከል ያሉ የሰላምና የልማት ግንኙነቶች ቀልጣፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ሰላም ለኢትዮጵያ!