ባህላዊ የሰላም ዕሴቶችን በመጠቀም የሕዝቦችን አብሮነትና ትስስር ማጠናከር ይገባል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ግንቦት 17/2017 (ሰላም ሚኒስቴር )፡-ባህላዊ የሰላም ዕሴቶችን አጎልብቶ በመጠቀም የህዝቦችን አብሮነትና ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ተናግረዋል ።

ሁለተኛው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልና የጋምቤላ ክልል የሰላምና የልማት ትብብር ፎረም በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ በወቅቱ እንደገለጹት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ባህላዊ እሴቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና አላቸው።

እነዚህን እሴቶች አጎልብቶ በመጠቀም የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት ከማጠናከር አንጻር በክልሎቹ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ይቅር ባይነትን ባህል በማድረግ በጋራ የማደግ ዕድልን ይበልጥ ማጠናከር እንዲቻል ባህላዊ የሰላም ዕሴቶቹን ማጠናከርና ከፍትህ ሥርዓቱ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) "ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጋራ ዓላማ ይዞ በጋራ መሥራትና በሕዝቦች መካከል የትብብር ዕሴትን ማዳበር ይገባል" ብለዋል።

የክልሎቹ ሕዝቦች ያላቸው አብሮ የመልማት ዕድልና ተቀራርቦ የመስራት ባህል እንዲሰፋ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ንግድና መሰል እንቅስቃሴዎችን በጋራ መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው ክልሎቹን የልማት ኮሪደር በማድረግ ሕዝቦችን በማኅበራዊና በኢኮኖሚ መስክ ማስተሳሰርና ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም የጋራ አቅጣጫ አውጥቶ ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአመራር ቁርጠኝነትን መላበስ እንደሚጠይቅ ገልጸው ለእዚህም መዘጋጀት ይገባል ብለዋል።

በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የሁለቱ ክልሎች የሰላምና የልማት ትብብር ፎረም መድረክ የፌዴራልና የሁለቱ ክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

#ኢዚአ