በአፋር እና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
በአፋር እና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሲከሰት የነበረውን ግጭት ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች በአካባቢው የነበረውን ግጭት በማስቆም ረገድ ውጤት እያመጣ እንደሆነ ግጭቱን ለማስቆም የተቋቋመው የፌደራል እና የክልል መንግስታት አብይ ኮሚቴ ስብሰባውን ባደረገበት ጊዜ ተገልጿል። በኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የፌደራል እና የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈው አብይ ኮሚቴ በቀን 18/06/2017 ስብሰባውን ያደረገ ሲሆን በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባለፉት ወራት ተኩስ እንዲቆም በማድረግ፣ በየደረጃው የሰላም ውይይቶችን በማድረግ፣ የተፈናቃዮችን መረጃ በማጥራት የተሰራው ስራ አመርቂ እና ለቀጣይ ስራዎችን መደላድል የሚፈጥሩ መሆኑን አመላክተው ለመጣው ውጤት የሁለቱን ክልል አመራሮች እና የቴክኒከ ኮሚቴውን አመስግነዋል። እስካሁን ግጭትን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማረገገጥ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ በተሰሩ ስራዎች በአካባቢዎቹ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፈን የተሰራዉን ስራ በማጠናከር ዘላቂ ማደረግ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ሁለቱ ማህበረሰቦች ለብዙ ዘመናት አብረው ከመኖራቸው፣ ካላቸው ማህበራዊ መቀራረብ እና የዳበረ የሰላም እሴት እንጻር መከሰት ያልነበረበት እንደሆነ አውስተዋል። አክለውም አሁን የተፈጠረው መቀራረብ እንደ እድል በመውሰድ ሁሉም በባለቤትነት ስሜት የሚሰራ እና ሌላውን ማህበረሰብ እንደራሱ በማየት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚተጋ ከሆነ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እስካሁን በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች መልካም ቢሆኑም፤ አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮችን በተለይም የተፈጠረውን ሰላም የማስፈን ስራ ህዝቡ በባለቤትነት እንዲይዘው በማድረግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የጋራ ስራዎችን በፍጥነት መተግበር ላይ ያለ ውስንነት እና አልፎ አልፎ የሚታዩ አንዳንድ ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮች በማረም ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራዎቻችንን መከወን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ እንዲሁም በአጠረ ጊዜ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲኖሩ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ በትኩረት እና በትጋት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን በመሻገር በሁለቱም ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ባለው ቅዱሱ የረመዳን ወር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ እና እርቀ ሰላምን የሚፈጥሩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።