የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁ ታላቅ ስኬት ነው። የሰላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤውን በሰላም በማጠናቀቁ ለብፁዓን አባቶችና የአምነቱ ተከታዮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ኢትዮጵያዊ አብሮነት እንዱሁም በሀገር ሰላም ግንባታ ሂደቶች እንደሌሎች የሀገራችን ሃይማኖቶች ሁሉ ጉልህ ሚና ስትጫወት የቆየች፤ አሁንም ይህንን ተግባሯን እያከናወነች እንዳለች ይገነዘባል። ለዚህም ልዩ አክብሮት አለን። ተቋማችን ከቤተክርስትያኒቷ ጋር የወል ግባችን ለሆኑት የሰላም እና የሀገር ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት ከምንግዜውም በበለጠ ያለንን ቁርጠኝነትም ለመግለፅ እንወዳለን። በጉባኤው ተመርጠው ኃላፊነትን ከተረከቡት አባቶች ጋርም ተቀራርበን ለመስራት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅን ቤተ ክርስቲያኒቷ በሰላም፣ በማኅበራዊ ልማት እና በሀገር ግንባታ የሚጠበቅባትን ሀገራዊ ኃላፊነት እንደምትወጣም ተስፋ እናደርጋለን ። በድጋሚ የርክበ ካህናት ጉባዔው ለሀገራችን ሰላምና ህብረ ብሔራዊ ግንባታ በሚያግዝ መልኩ በሰላም በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን።
ሰላም ለኢትዮጵያ!
ግንቦት 20/2017 ዓ.ም
ሰላም ሚኒስቴር