ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት ለዘላቂ ሰላም
ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት ለዘላቂ ሰላም
በሀገራችን ብዙህነትን እውን ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ በህብረ ብሄራዊ የፈዴራል ስርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ፤ መግባባት እና የአመለካከት የበላይነት በሁሉም ደረጃ ማረጋገጥ ይገኝበታል፡፡ በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓታችን ውስጥ በተፈጥሮ ያለው ልዩነት በሥራና በሂደት ወደ ብዙህነት ሲያድግ፤ ህብረ ብሄራዊነታችን በተግባር፤ በሥራ ሲረጋገጥ ሀገራዊ ውበታችንና ኩራታችን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስለ ብዝሃነት መስረታዊ መነሻና መድረሻ በአግባቡ መረዳትና ማስረዳት ሚናው ከፍተኛ ነው::
በመጀመሪያ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተፈጥሮ የሚገኝ በዓይነት ወይም በልዩነት ላይ የተመሰረተ የቁጥር ብዙነት ብቻ ሳይሆን ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት፣ የውበትና የጥንካሬ ምንጭ ለማድረግና ለማጎልበት በቁርጠኝነት በመስራት የሚረጋገጥ የጥምረት እና የጥረት ውጤት የሆነ ህብር ነው፡፡ እንዲሁም በሀይማኖቶችና ተቋሞቻቸው በብሄር፣ ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት በመቻቻል፤ በመከባበርና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህብረት እንዲሆን ለማድረግ በሚፈጠረው መልካም ግንኙነት የሚረጋገጥ የአብሮነት ውጤት ነው፡፡ ብዙህነት እንደ ልዩነት በተፈጥሮ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተጨባጭ እንዲኖርና አንዲረጋገጥ ለማድረግ ስራን እና ጥረትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም አኳኋን ሲገነባ በህብረ ብሄራዊ ስርዓት ውስጥ ያለው ልዩነት የውበትና የአብሮነት ማሳያ/መገለጫ ይሆናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ብዙህነት መቻቻል ማለት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶቻችንን በፈጠሩት እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶቻችን ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ (መረዳዳትን) መፍጠር ነው፡፡ መቻቻል ለአብሮነት የሚያስፈልግ የጋራ እሴት ቢሆንም ተቻችሎ ለመኖር ግን አንዱ የሌላውን እምነት ምንነት እና ማንነት በጥልቀት ማወቅ አስገዳጅ አይደለም፡፡ የማንነት እና የሀይማኖት ጥንቅሯ ብዙ በሆነባት አለማችን ውስጥ መቻቻል ብቻውን ቁንፅል የሆነ እና ጨለምተኝነትንና ቅድመ-ቅኝት (Stereotypes) ለማስወገድም በራሱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በተለያዩ ማንነቶች እንዲሁም ሀይማኖቶች መሀል ሊወገድ የሚገባው ጨለምተኝነት እስካለ እና እስካልተወገደ ድረስ ጊዜያትን ቆጥሮም ቢሆን በአሉታዊነቱ ዋጋ የሚያስከፍል እዳ ሊሆን ይችላል፡፡ ጨለምተኝነት ደግሞ መወገድ የሚችለውና የሚገባው ባማሩ ቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር በተረጋገጠ ቁርጠኝነት እና የስራ ውጤት ወይም መስዋዕት ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተለያዩ ሁኔታዎች በአጋጣሚ የሚፈጠር አንፃራዊነት እና እንደየሁኔታው የሚለያይ/የሚቀያየር ሳይሆን በማንኛውም ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ የግድ ዋጋ ወይም መስዋዕት የሚከፈልለት/የሚከፈልበት ነው፡፡ ብዙህነት ዋጋ የሚከፈልለት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ብዙህነትን አስመልክቶ ያለ የአቅጣጫ ምልከታና እርምጃ የማንነት መገለጫዎቻችንን እንድንተው የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ለአብሮነታችን ሲባል በሀይማኖቶች፣ በብሄር፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች ወይም ማንነቶች መሀል ያሉ ልዩነቶቻችንን መተው ወይም መካድ ሳያስፈልግ የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ ግንኙነቶችን በመፍጠርና በማጠናከር አንድነትንም ጭምር ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡
ስለሆነም ብዙህነትን የውይይት፤ የድርድር እንዲሁም የሰጥቶ መቀበል ባህል መጎልበት ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብዙህነት ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ድርድርን፤ የጋራ መረዳዳትን እና ግንዛቤ የሚፈልግ ሂደት(ሥርዓት) ነው፡፡ ስለሆነም በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋራቸው መደበኛ ያልሆኑ መግባቢያዎች ጭምር ህብረ ብሄራዊነትን የሚያከብሩና የሚያንፀባርቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡
የብዙህነት መረጋገጥ እንደ እኛ ላለ ህብረ ብሄራዊ ሀገር የዘላቂ ሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ማስፈኛ ወሳኝ መሰረት መሆኑን በሚገባ አውቀን የበኩላችንን ድርሻ የመወጣት ሀላፊነት አለብን፡፡