“በጎነት ለአብሮነት”
“በጎነት ለአብሮነት”
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት መካከል ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ የባህል ልውውጥ ስራዎችን እንደሚያከናውንና በህብረተሰቡ መካከል የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር የግንዛቤና ንቅናቄ ስልቶችን በመቀየስ እንደሚሰራ ተቀምጧል። ተቋማችን ከላይ በአዋጅ የተሰጡት ተግባራት ለማካናወን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ “በጎነት ለአብሮነት” በሚል ፅንስ ሃሳብ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በመንደፍ በርካታ ወጣቶችን እያሳተፈ ይገኛል፡፡
ፕሮግራሙን ከዘላቂ ሰላም እና ከሀገር አንድነት ጋር በማስተሳሰር ስራዎችን መስራት ከተጀመረ 12ተኛ ዙሩን ይዟል፡፡ ይህ ፕሮግራም በታሪክ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩ እና የተዛነፉ ትርክቶችን ለማስተካከል ወጣቶችን ከሚኖሩበት አካባቢ ወጥተው ወደ ማያውቁት አካባቢ/ክልል/ በመሄድ የማያውቁትን ማህበረሰብ እንዲመለከቱ፣ሌላኛውን የኢትዮጵያ ጫፍ በእግራቸው ረግጠው በአቅማቸው አገልግለው የሀገር ፍቅርን እንዲያዳብሩ እና በሂደቱ ደግሞ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ወንድማማችነትን እንዲጠናክሩ የተቀየሰ እና እየተሰራበት ያለ ፕሮግራም ነው፡፡
የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ ኢትዮጵያ ያሏትን መልካም እሴቶች፣መርሆዎች፣ የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ የወጣቶችን ምክንያታዊነትን፣ የሕይወት መምራት ክሕሎትን፣ የሥራ ባሕልን፣ መልካም ሥነ ምግባርን በማጎልበት አገራዊ አንድነትን እና ብሔራዊ መግባባትን በማስረጽ ዘላቂ ሰላም መገንባት የሚያስችል ነው ፡፡
ብሄራዊ ስሜትና ኩራት እንዲሁም የኢትዮጵያ አንድነትን የተረዱ፣ በራስ መተማማናቸው ያደገ፣ ብቁ ፣ ተወዳዳሪ እና ማህበረሰብ ተኮር ባህሪን ያዳበሩና በሀገር ግንባታ ውስጥ ገንቢ በሆነ መንገድ ለመሳተፍ ዝግጁ የሆኑ ውጤቶች መፈጠር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም ካስገኛቸው ዋና ዋና ውጤቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!