ሊሂቃን ለሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
ሊሂቃን ለሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
ታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጋር በመተባበር “የልሂቃን ሚና ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሀገር ግንባታ ሥራ የሁሉንም ተሳትፎ እና ርብርብ ይጠይቃል ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ይህን ማንነታችንን ለመለያየት ሳይሆን ለአንድነት እና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ልናውለው ይገባል ብለዋል፡፡
ያሉብንን ሀገራዊ ችግሮች በውይይት፣ በምክክርና በድርድር በመፍታት ዘላቂ ሰላማችንን እና ልማታችንን ልናፋጥን ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የዛሬው መድረክ ዓላማ "ሊሂቃን በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ክቡር ፓስተር ፃድቁ አብዶ በበኩላቸው ሀገር የሚገነባው ዕውነተኛ መከባበር እና ፍትህ ሲኖር መሆኑን ገልፀው የሀገር ግንባታ ሥራ በየጊዜው የሚሰራ እና ክትትል የሚፈልግ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የሀገራችን አብዛኛው ችግር የሊሂቃኑ ችግር ነው ያሉት ፓስተር ፃዲቁ ሊሂቃን ለሀገር ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ለተግባራዊነቱ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
“ሀገር ግንባታ እና የሊሂቃን ሚና በኢትዮጵያ” የሚል ሰነድ የሲንአርአይኤስ ዋና ዳይሪክተር (Executive Director of CENRIS) በሆኑት በዶ/ር ሙሉሸዋ ኢብራሂም በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመድረኩ ላይ “የሰላም ግንባታ ማሰልጠኛ መፅሐፍ” የተመረቀ ሲሆን የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጋር በሀገር ግንባታ እና በሰላም ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ተፈራርመዋል፡፡