ማህበራዊ ሃብቶች ለዘላቂ ሰላማችን መስፈን ያላቸው ዋስትና

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ኢትዮጵያዊያን አብሮ በመኖር ባደረጓቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማስተጋብሮች ያካበቷቸው ዘመናትን የተሻገሩ ድንቅ ማህበራዊ ሃብቶችና ዕሴቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡

በመላው የሀገራችን ክፍል የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዕርቅና ሰላምን ለማምጣት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ የሽምግልና ስርዓት ነው፡፡ይህ ስርዓት በተለያዩ ስያሜዎች በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት እስካሁን ድረስ በስፋት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ለአብነትም በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የአስተዳደር፣የሕግና የፍትሕ የሆነው የገዳ ሥርዓት ውስጥ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት የሚያገለግሉት ጉማና ስንቄ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይም በአማራ ማህበረሰብ ዘንድ የሚዘወተሩት የሽምግልና፣የዘወልድና የአበጋር ስርዓቶች፣ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ እርቅ የሚፈፀምበት የጆካ ስርዓት፣ በጋሞና በሲዳማ አባቶች የሚከወኑ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶች ጥቂቶች የማህበራዊ ሃብቶች ናቸው፡፡

የሰላም ሚኒስቴር እነዚህን የመሳሰሉ ነባር ማህበራዊ ሃብቶች እና ዕሴቶች ለሰላም ግንባታና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን በመጠቀም ረገድ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ዘላቂ ሰላማችንን ለማስፈን እና የተረጋጋች ሀገር እንድትኖረን ለማድረግ አዲስ የሰላም አስተሳሰብ ቀርፆ እየሰራ የሚገኘ ሲሆን ይህም የሰላም እሳቢያችን ከሰላም አውድ ትንተና የሚነሳ፣ በኢትዮጵያዊ ማህበረ ባህላዊ ዕሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ለአወንታዊ ሰላም ግንባታ ቅድሚያ የሚሰጥ እና ግጭት ቅድመ መከላከል እና የግጭት ዘላቂ መፍትሔ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡

አወንታዊ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻለው ግጭቶች በተፈጠሩ ቁጥር በሚወሰዱ እርምጃዎች ብቻ ሳይሆን የዜጎች የዕለተለት ሕይወት ውሰጥ መተማመንን፣ትብብርን፣አብሮነትን የመሳሰሉ ዕሴቶችን በማጎልበት በኩል ጉልህ ፋይዳ የሚጫወቱ ማህበረ ባህላዊ ተቋማትን በማጠናከር ነው።

የሰላም ፣እርቅ፣ አብሮነትና መደጋገፍ የተሰኙ ማህበረ ባህላዊ ተቋማት ጠንካራ በሆኑባቸው አካባቢዎች ወይም ማህበረሰቦች ዘንድ ሰላም ማስፈን አልፎ አልፎ ግጭቶችና አለመግባባቶች ቢፈጠሩም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻል እሙን ነው፡፡

ማህበራዊ ሃብቶቻችን በማጠናከር የሰላም ሥራን በዘወትር ሕይወት ውስጥ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ አወንታዊና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ያስችላል፡፡ይህን በማድረግ ጥረት ውስጥ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ማህበረ ባህላዊ ሀብቶችን መለየት ፣ መሰነድ፣ማጥናት፣ ማስታዋወቅ ፣መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!