በአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት 13ኛ ዙር የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተጀመረ
በአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት 13ኛ ዙር የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተጀመረ
ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት 13ኛ ዙር የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና መክፈቻ መርሐ-ግብር በአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ ተከናውኗል፡፡
በመክፈቻ መርሐ-ግብሩን የከፈቱት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ሀገራዊ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆዎችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በብሔር ብሔረሰብ፣ በሀይማኖት፣ እና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለው ልዩነት ጌጥ እንጂ ዕዳ አለመሆኑን በመገንዘብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት በተለይም የወጣቶችን የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል “ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ የማይተካ ሚና እንዳላችሁ ተገንዝባችሁ ምንጫቸው በማይታወቅ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከሚተላለፉ ዜጎችን ከሚያራርቁ አፈራሽ ዘገባዎች እራሳችሁን እንድታርቁና ዜጎችን የሚያቀራርቡ፤ ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱ ይዘቶችን በማሰራጨት ኃላፊነታችሁን መወጣት ይኖርባቸዋል”፤ በማለት ለሰልጣኞች መልእክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ለሀገራዊ “ሰላማችን መረጋገጥ ሁላችሁም ፍትሐዊነትን በማስፈን የምታምኑ፤ የሀገረ-መንግሥት ግንባታን የምታጠናክሩ፤ የግብረገብነትና የሰላም እሴቶችን የምትሰብኩ፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ፍቅር ያላችሁ፣ ብዙኃነትን የምትቀበሉ፣ ሰብአዊ መብቶችን የምታከብሩ፣ በምክንያታዊ ትንተና እና በውይይት የምታምኑ እንድትሆኑ አደራ”፤ ሲሉም አክለዋል፡፡
