"ግጭት ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፍና ለውጭ ጠላቶቻችን ተጋላጭ የሚያደርግ ነው።" ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
"ግጭት ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፍና ለውጭ ጠላቶቻችን ተጋላጭ የሚያደርግ ነው።" ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ
መጋቢት 17ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሱማሌ እና አፋር ክልሎችን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የተጀመረው የውይይት የክልሎቹን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመግባባት ተጠናቀቀ።
ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የጎሣ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎች በተገኙበት የሁለቱን ሕዝቦች ሰላማዊ ግንኙነት ለማጠናከር ሲደረግ የቆየው ምክክር በክልሎቹ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል ባሉት ጉዳይ በጥልቀት መክረዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይህ ሰላምን የማፅናት መድረክ ቀደም ሲል በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት በሰላማዊ ውይይት መቋጫ እንዲያገኝ በተደረገው ርብርብ የመጣው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ በማኅበረሰቦቹ መካከል ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ጠብቆ የጋራ ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከር መተኮር ያለባቸው አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። የሁለቱን ክልሎች ሰላምና ልማትን ለማጠናከር የሚሠራ የጋራ ፎረም ተቋቁሟል።
በውይይት መድረኩ ማጠቃለያና የፎረም ምሥረታው ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሐመድ እድሪስ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። "ሁለቱ ማኅበረሰቦች ፍፁም የማይነጣጠል የጋራ ታሪክ ያለቸው ፤ እንኳን የሚያጋጫቸው የሚያኮራርፈቸው አንዳችም ምክንያት ሳይኖር እየተከሰተ የታየው ግጭት ፎጹም መከሰት የሌለበት፤ የሚቆጭ እና ዳግም መከሰት የሌለበት ነው" ፤ ሲሉ አሳስበዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ የፎረሙን መመሥረት አስመልክተው ባሰሙት ንግግር ፎረሙ የሁለቱንም ክልሎች ሰላም እና ልማት ለማሳለጥ ማኅበረሰቦችን በወከሉ አባላት የተቋቋመ ፎረም በመሆኑ ትልቅ ውጤት የሚጠበቅበት ልዩ ፎረም መሆኑን አመላክተዋል። በሚኒስቴሩ ፣ በመንግሥት እና አጋር አካላት የሚደገፍ ፎረም መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፎረሙ አብሮነት እንዲገነባና የጋራ ብልፅግና ትልም ግቡን እንዲመታ ጠንክሮ እንዲሠራ ክቡር ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፉዎችም ለግጭት የሚያደርሰውን ችግር ማወቅና ከመሠረቱ ችግሩን አስወግዶ መፍትሔ በማምጣት ሲገባን ለመጪ ትውልድ የግጭትን እና ድህነትን በማውረስ የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን ካለፈው ተምረን የተረጋጋ ሰላምን ለመፍጠር ቁርጠኛ ለመሆን መወሰናቸውን ገልፀዋል።