የመንግስታት ግንኙነት
የመንግስታት ግንኙነት
የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር መካከል በመንግስታት መካከል ያሉትን ግንኙነቶች በመከታተል ክፍተቶችና ችግሮች ለይቶ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና በአሰራር በመደገፍ እንዲሁም ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን (ግጭቶችን) በድርድር፣በመተባበበር እና በአጋርነት እንዲፈቱ ማድረግ አንዱ ነው።
ችግሮች ሲከሰቱ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዳበረና ቀጣይነት ያለው የፌደራል ስርዓትና የተጠናከረ የመንግስታት ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ሌላው የተቋሙ ተግባር ነው።
ከላይ የተቀመጡትን ተግባራት ለማከናወን ደግሞ የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት ሚና አይተኬ ነው ። የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል፣ እንዲሁም በክልሎች መካከል የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር ማስቻል ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት ዓላማ የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ ማስጠበቅ፣ ጠንካራ የሕዝቦች ግንኙነትና ትስስር መፍጠር፣ ሃገራዊ እና ክልላዊ ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲፈፀሙ ለማድረግ እንዲሁም በመንግስታት መካከል ያሉ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ በአጋርነት ላይ የተመሰረተ የአመራር መርሆ በማስፈን በጋራ የሚመሩበትና የሚመክሩበት ስርዓት መገንባት ነው።
የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓቱን ለማጠናከርና ቀጣይነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተቋማዊ ስርዓት ለመፍጠር እንደ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
ከዚህ በተጨማሪም በፌዴራል መንግስትና በክልሎች እንዲሁም በክልሎች መካከል እርስ በርስ የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈቱበትን የግንኙነት አግባብ መዘርጋትና ማጠናከ ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራል ስርዓቱ ሞተር መሆኑን በማመን በፌዴራልና በክልል እንዲሁም በክልሎች መካከል ያሉ የሰላምና የልማት ግንኙነቶች ቀልጣፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ሰላም ለኢትዮጵያ!