የክረምት ልዩ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ጉብኝት ተደረገ
የክረምት ልዩ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ጉብኝት ተደረገ
የሰላም ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የክረምት ዕረፍት ጊዜያቸውን በበጎ ፈቃድ ስራዎች ተሰማርተው ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ለሀገር ግንባታ እና ህብረብሔራዊ አንድነትን የበኩላቸውን አስተዋጾኦ እንዲያበረክቱ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን "ብዝሃነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩ ይታዎቃል።
በዚህም መሰረት ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የክረምት ልዩ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ጉብኝት ተደረጓል፡፡
በጉብኝቱ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም “የክረምት ልዩ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከተወለዱበትና ካደጉበት አካባቢ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠት ኢትዮጵያዊ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ ማኅበራዊ እሴቶችን እና ብዝኃነትን በመገንዘብ ዕርስ በርሳቸው የሚተዋወቁበትና ሀገራቸውን የሚያውቁበት፤ የአብሮነት መስተጋብርን አጠናክረው በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አሻራ የሚያሳርፉበት ሀገራዊ መርሐ ግብር ነው” ብለዋል።
የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) “ሀገራዊ መርሐ ግብሩ ወጣቱን በማቀራረብ ዕርስ በዕርስ የሚያስተዋውቅ፣ በዜጎች መካከል የተፈጠረውን ጥርጣሬ በማጥፋት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚያጎለብት እና ከአካባቢያዊ ማንነቱ ባሻገር ወሰን ተሻጋሪ አስተሳሰቦችን አጎልብቶ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ለሁሉም ሀገሩ መሆኑን እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች በአካባቢ የታጠረ እሳቤን ሰብረው ድንበር ተሻጋሪ አስተሳሰብ በመያዝ፣ የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ሀገራዊ እሴቶችን እንዲያጎለብቱ፣ ለማኅበራዊ ትስስራችን እና ለሀገራዊ አንድነታችን መጠናከር ሚናቸውን እንዲወጡ ጉብኝቱን ያደረጉ ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች አሳስበዋል፡፡