የታሪክ ሙሁራን ለሀገረ መንግስት ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
የታሪክ ሙሁራን ለሀገረ መንግስት ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር "ታሪክን ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ " በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ፤ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አገር አቀፍ ጉባኤ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱአለም የሰላም ሚኒስቴር ከተሰጡት ተልዕኮ መካከል የሀገር ግንባታ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መተግበር እንደሆነ ገልጸዋል።
የሀገር ግንባታ ሥራ ከታሪክ አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘና ያለ ታሪክ የሀገረ-ግንባታ ሥራ አይታሰብም ብለዋል።
የሀገር ግንባታና ታሪክ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለሀገር ግንባታ ቁልፉ መሳሪያ ታሪክ ሲሆን በሀገራችን ዛሬ ላይ ለሚስተዋሉት አለመግባባቶች ምክንያቱ ታሪክን በአግባቡ አለማስረጽ ነው ብለዋል፡፡
ታሪክ ከታሪክ ባለሙያዎች እየወጣ በጥቅም ፈላጊ ፖለቲከኞች እየተዘዋወረ ሲሆን የታሪክ ምሁራንም ታሪክን ወደ ባለቤቱ በመመለስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ማህበሩ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።
ማህበሩ የተለያዩ መጽሐፍቶችን ማሳተሙን ገልጸው፤ ታሪክ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩሉን እያበረከተ መሆኑንም ገልፀዋል። በመድረኩ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና የብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ታሪኮቻችን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያካትት እና አስተማሪ እንጂ አነታራኪ እንዳይሆን መስራት እንዳለብን አደራ ብለዋል።
ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የሁላችንም ሀላፊነት በመሆኑ በተለይም የታሪክ ሙሁራን የሰላም አርበኛ በመሆን እንዲሰሩም አሳስበዋል።