በአርብቶ  አደሮች  አካባቢ  የሚከሰቱ  ግጭቶችን  በጥናት  በመለየት  መፍትሄ  ማበጀት  ያስፈልጋል  ተባለ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ግንቦት 28/2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  በሚገኙ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች  አካባቢዎች  እየተከሰቱ በሚገኙ ግጭቶች መንስዔዎቻቸው እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ  ከጎሳ መሪዎች፣ ከህብረተሰብ ተወካዮችና እና ከሰላምና ፀጥታ አመራሮች ጋር  በጅንካ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ  በዞኑ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከጎሳ መሪዎች፣ ከህገር ሽማግሌዎች እና ከኃይማኖት አባቶች ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ይህ መድረክ በቀጣይ  የሚሰሩ ሥራዎች  ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች  ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ አንቄ በበኩላቸው  በክልሉ በሚገኙ አርብቶ አደሮች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል  ትልልቅ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልፀው  በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት ለመስራት እንደዚህ አይነቱ  ውይይት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት  ከሰላም ሚኒስቴር ከግጭት አስተዳዳር ዘርፍ የመጡት አቶ ታደሰ ሜጋ  የሰላም ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል  የመንግስታት ግንኙነትን ማጠናከር፤ የህዝብ ሰላም መጠበቁን ለማረጋገጥ አግባብነት ካላቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት አካላት ጋር በመተባበር መስራት፤  እንዲሁም በተለያዩ የአገርቱ  አካባቢዎች የግጭት ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት ለአካባቢያዊ ግጭቶች መንሳኤ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት መለየት መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም  ህብረተሰቡ ወደ ግጭትና አለመግባባት  እንዳያመራ የመፍተሄ አቅጣጫዎችን የሚያመለክት ጥናት በማካሄድ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማቅረብ እና ሲወሰን  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን  ስልቶችን ቀይሶ መተግበር መሆኑን ገልፀዋል።

የዛሬው  የምክክር መድረክ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በደረቅ እና በእርጥበት ወቅቶች የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን/ግጭቶችን/ ለመቀረፍ የሚያስችል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር ወደ መፍትሄ የሚያደርሱ ሃሳቦችን  ለማሰባሰብና ለማደራጅት  ታሳቢ ያደረገ  መሆኑን አቶ ታደሰ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ  ''የመንግስታት ግንኙነት አዋጅ አተገባበርና አስፈላጊነት'' የሚል ፅሁፍ በሰላም ሚኒስቴር የመንግሥታት ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ግርማ ቸሩ  እንዲሁም '' ግጭት ማስተዳደርና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት '' የሚል ፅሁፍ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር  የግጭት ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አለኸኝ ገሪማ በኩል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።