ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ውይይት ተደረገ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በግጭት መከላከል፣ የግጭት ተጋላጭ አካባቢዎችን ወደ ዘላቂ ልማት ማሸጋገር እና "የወጣቶች በጎ ፈቃደኝነት ለሰላም" ፕሮጀክቶች ላይ ውይይት ተደረገ፡፡

ውይይቱ በሚኒስቴሩ የተቀረጹ የቀጣይ 10 ዓመታት የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፕሮግራም እና ከዚሁ በሚመነጩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የዓለም አቀፍ አጋር አካላትን ሚና አቀናጅቶ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩትን የሰላም ችግሮች ለመፍታትና ዘላቂ የሆነ አዎንታዊ ሰላም ለመገንባት መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የመልክዓ-ምድር፣ የቋንቋ፣ ብዝኃነትን ተጠቅማ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትብብርና ድጋፍ የሚጠይቁ መሆኑን ጠቅሰው ለዚሁ አስፈላጊውን የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፌደራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ሚኒስቴሩ ግጭቶችን ለመፍታት፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለማቋቋምና ወደ ነበሩበት ቀዬ ለመመለስ ብሎም ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ከምንጩ መፍትሔ ለመስጠት በሁሉም ክልሎች እየተሠራ ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማጠናከር ሥራ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለዚህም የዓለም አቀፍ አጋር አካላት ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የአለም አቀፍ ተቋማትና የተለያዩ ሀገራት ኢምባሲ ተወካዮች በኩላቸው የዛሬው መድረክ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር ለመተዋወቅ እንዲሁም በቀጣይም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያከናውናቸው የሰላም ግንባታና በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ በሚደረገው እንቅስቃሴ በትብብር ለመስራትና መንግስት አዎንታዊ ሰላምን ለመገንባት የሚያደርገውን እንቅስቀሴ በቅርበት ለመረዳት እንዳገዛቸው ገልጸዋል ።