የ13ኛ ዙር በጎ ፈቃደኞች ተመረቁ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ሰኔ 4/2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በ13ኛው ዙር መርሃ ግብር ሲያሰለጥናቸው የቆዩትን የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ተሳታፊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አስመርቋል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ለተመራቂ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መልዕክት ያስተላለፉት በሚኒስትር ዴዔታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ በማድረግ ፤ በማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን አለመግባባት በማስወገድ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ወጣቶች ማህበረሰባዊ እሴቶችን እና የሞራል አቅም እንዲያጎለብቱ በመደገፍ በተለይም ብዝሃነት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ እርስ በርስ መደማመጥንና መረዳዳትን ከማምጣት አንፃር ሚናው የጎላ ነው ያሉ ሲሆን አንዱ የሌላውን እሴቶችንና ባህል እንዲያውቅና እንዲያከብር ግንዛቤን ያሳድጋል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ወጣት ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራት መሆኑን በማመን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የወጣቶች የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በመንደፍ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ካይዳኪ በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም የተሳተፉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመላው ሀገሪቱ የሰላም አምባሳደሮች ሆነዋል፣ ህዝብ የማቀራረብ ስራ ሰርተዋል፣ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እንዲዳብሩ አድርገዋል፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስሜት ከፍ እንዲል የተለያዩ ተግባራትን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጌታቸው ዓለሙ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰላም፣የብዝሃነት፣የአንድነት እና የእኩልነት ሀገር ሆና እንድትቀጠል የበጎ ፈቃድ ስራ በእጁጉ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን ዛሬ የተመረቃችሁ የሰላም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለዩኒቨርስቲያችን ውበትና ኩራት ነበራችሁ፤ በሄዳቹሁበት ሁሉ የሰላም አምባሳደር ሁናችሁ እንድታገለግሉ ጥሪ አስተላልፋለሁ ብለዋል።

ወጣቶች ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራት ነው ያሉት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ መንግሥቱ ላሉ ናቸው። አቶ መንግስቱ የሰላም ሚኒስቴር ወጣቶች ላይ እየሰራው ያለውን ስራ አድንቀው ቢሮው የበጎ ፈቃደኛ የወጣቶችን የቀጣይ የስምሪት ሂደት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩም ላይ የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ፣ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።