ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ውጤታማ መንገድ ተቀራርቦ መነጋገር ነው

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (የሰላም ሚኒስቴር) በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር ግጭቶችን አስወግዶ ሰላምን ለማፅናት፣ ኅብረተሰቡን የሚያቀራርቡ ማኅበራዊ ተቋማትን በጋራ ለማልማት እና አብሮነትን ለማጠናከር በትብብር ለመሥራት በመወሰን ተጠቃሏል፡፡

ለግጭት መንስዔ የሚሆኑ ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመር ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሀይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሰላምና የልማት ፎረም አባላትን እና የክልሎቹን የሰላምና ፀጥታ አመራሮችን በማሳተፍ ለሁለት ቀናት የመከረው የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ በክልሎቹ አንዳንድ አካባቢዎች ከነበሩ ሁኔታዎች አንፃር ለዘላቂ መፍትሔ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝም እና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ግጭቶችን አስወግዶ አዎንታዊ ሰላምን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ መንግሥት ሕዝብን ያሳተፈ የመፍትሔ አቅጣጫ መከተሉን በአፅንዖት በመግለፅ መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ አቅጣጫ የሚጥሉት የሰላም መሠረት ዘላቂ እንደሆነ ስለሚታመን መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ውጤታማ መንገድ ተቀራርቦ መነጋገር መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በመድረኩ የተገኙት የማኅበረሰብ ተወካዮች በየማኅበረሰቦቻቸው ውስጥ ያለውን ቁርሾ በማስወገድ መጪው ጊዜ የግጭት ዜና የማይሰማበት ለትውልዱ ሰላም የሰፈነበትን ሀገር የሚያወርሱበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

“ትናንት ያለፈውን የግጭት ታሪክ እና የማይጠቅመንን ነገር እያሰብን መጪውን መልካም ዕድል እንዳናበላሽ ሁላችንም የሰላም አምባሳደር በመሆን ለልጆቻችን የሰላም መሠረት መጣል አለብን”፤ ሲሉም አክለዋል፡፡

የአፋር ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን መሐመድ “ከየትኛውም ወገን አንዳችን ለአንዳችን የግጭት መነሻ እንዳንሆን ከውስጣችን በመነጨ ቁርጠኝነት ተነስተን ለሰላም ከቆምን እና ሁላችንም በየአካባቢያችን ኅብረተሰቡን ስለሰላም ካስተማርን አሁን ያለው አንፃራዊ ሰላም እያደገ ስለሚሄድ በምንፈልገው ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን”፤ ብለዋል፡፡

የሱማሌ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብልቃድር ረሺድ ዱአሌ በበኩላቸው የሰላም ጉዳይ የሕዝብ ወይም የመንግሥት ተብሎ ለአንድ ወገን የማይተው እና ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብና ሁሉም በየደረጃው ሊቆምለትና ጥበቃ ሊያደርግለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በማብራረት ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ለጋራ ሰላም በጋራ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በየአካባቢው ለግጭት መነሻ የሚሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከል ክልሉ ከመንግሥትና ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በጥብቅ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎችም የሰላም እሴቶቻችንን ለተተኪው ትውልድ በማስተማር አብሮነትን ለማጠናከር ተግተው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡