የ12ኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኝ ወጣቶችን በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ አስመርቋል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በ12ኛው ዙር መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን የሰላም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ አስመርቋል።

የምረቃ ስነ ስርዓቱ በሃይማኖት አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች ፀሎትና ምርቃት ተጀምሯል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ለተመራቂ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ክቡር አቶ መሀመድ እድሪስ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አግልግሎት ፕሮግራም ወጣቶች ማህበረሰባዊ እሴቶችን እና የሞራል አቅም እንዲያጎለብቱ በመደገፍ በተለይም ብዝሃነት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር ውስጥ እርስ በርስ መደማመጥንና መረዳዳትን ከማምጣት አንፃር ሚናው የጎላ ነው ያሉ ሲሆን አንዱ የሌላውን እሴቶችንና ባህል እንዲያውቅና እንዲያከብር ግንዛቤን ያሳድጋል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ወጣት ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራት መሆኑን በማመን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የወጣቶች የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም በመንደፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው በፕሮግራም የተሳተፉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመላው ሀገሪቱ የሰላም አምባሳደሮች ሆነዋል፣ ህዝብ የማቀራረብ ስራ ሰርተዋል፣ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እንዲዳብሩ አድርገዋል፣ ብዝሃነትን እንደ በጎ እድል የመቆጠር ሃሳብ አድጓል፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስሜት ከፍ እንዲል የተለያዩ ተግባራትን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተከበሩ ወ/ሮ አስቴር በሽር "በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሐሳብ በሰላም ሚኒስቴር የተጀመረው የሰላም የወጣቶች በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዓላማ የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ በማድረግ ፤ በማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን አለመግባባት በማስወገድ የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤርሚያስ ሞሊቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰላም፣የብዝሃነት፣የአንድነት እና የእኩልነት ሀገር ሆና እንድትቀጠል የበጎ ፈቃድ ስራ በእጅጉ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን ዛሬ የተመረቃችሁ የሰላም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለዩኒቨርስቲያችን ውበትና ኩራት ነበራችሁ፤ በሄዳቹሁበት ሁሉ የሰላም አምባሳደር ሁናችሁ እንድታገለግሉ ጥሪ አስተላልፋለሁ ብለዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩም ላይ የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ፣ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።