የሰላም ሚኒስቴር በ12ኛው ዙር ያሰለጠናቸውን የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞችን አስመረቀ
የሰላም ሚኒስቴር በ12ኛው ዙር ያሰለጠናቸውን የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞችን አስመረቀ
መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰላም ሚኒስቴር) የሰላም ሚኒስቴር ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ12ኛው ዙር ፕሮግራም ለሀያ ሁለት ቀናት በጅማ ዮንቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን ከአንድ ሺህ 200 በላይ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ፈቲሂ መሂዲ "በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የወጣቶች በጎ ፍቃድ የማህበረሰብ አግልግሎት መርሃ ግብር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እና መርሆዎችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት እና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ በማስወገድ የወጣቶችን የሀገር እና የሕዝብ ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የተከበሩ ዶ/ር ፈቲሂ አክለውም "በዛሬው እለት የስልጠና ጊዜያችሁን አጠናቃችሁ ስምሪት የሚሰጣችሁ በጎ ፈቃደኞች በበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ላይ መሳተፍ ዕድለኝነት እና የህሌናና የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ በዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት ስራ ውስጥ የራሳችሁን አሻራ እንድታሳርፉ አሳስባለሁ" ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው "እኛ ኢትዩጵያዉያን ፣ በርካቶች የሚመሰክሩት ፣ ከአለም ሀገሮች የሚለይ ባህል እሴት እና ማንነት ያለን ሲሆን ፣ ይህንን እሴታችንን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ቢሆንም ከወጣቶች ብዙ ይጠበቃል" ብለዋል።
በሀገራችን ያሉ አለመግባባቶችን በመተው ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ማጠናከር በልማት ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በምርምርና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ባህል ልናዳብር ይገባል፤ያሉት ዶ/ር ጀማል ከናንተ ብዙ የሚማሩ በብዙ የሚያተርፉ በርካቶች ናቸውና ከሰውነት ሳትጎድሉ ሀገራችሁ የሰጠቻችሁን ሀላፊነት እና የዜግነት ግዴታችሁን በሙሉ ኢትዮጵያዊ ልብ እንድትተገብሩ አደራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡